ግንቦት 20 የኢሕኣዴግ ብቻ በዓል እንጂ ህዝቡን ኣይመለከትም

ግንቦት 20 የኢሕኣዴግ ብቻ በዓል እንጂ ህዝቡን ኣይመለከትም

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ

የሕወሓት/ኢሕኣዴግ ስርዓት ከተቀጣጠለበት የህዝቦች ተቃውሞ የተነሳ እንደለመደው መጓዝ ስለተሳነው የግለሰቦች ለውጥ ለማ ድረግ ተገድዷል። በዚህም ዶር. ኣብይ ኣህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ተሹሟል። ይህ ጠ/ሚ ከኢሕኣዴግ ሹማምንት መካከል “ተመርጦ” መሾሙን እሱም ሆነ ህዝቦች ኣሳምረው ያውቃሉ። ወክሎት የመጣው የኦፒዲኦ/ኢህኣዴግ ድርጅት በኦሮሚያ የኢሕኣዴግ ወኪል በመሆን ላለፉት 27 ዓመታት በህዝቦች ላይ በተለይም ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲያደርስ የነበረው ጉዳት የማይረሳና ኣብሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ይህንን ዘንግተው ህዝቦች የሚሹትን ለውጥ ለማስገኘት ይሰራል ብሎ መጠበቅና ተስፋ ማድረግ “ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ” ከሚሉት ብሂል አይለይም።

ከዚህም ሌላ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲና ለሃገር ባለቤትነት መብት ተፋልመው በፍልሚያው ውስጥ የወደቁትን ተገቢውን ቦታ መንፈግ ወይንም የከፈሉትን መስዋዕትነት ጥላሸት መቀባት ኣልያም ማጥቆር ይሆናል። ለውጥ እናስገኛለን በሚል በህዝቦች ላይ የሚደሰኮረው ሁሉ ጊዜ ለመሸመትና በህዝቦች ትግል ከውድቀቱ ኣፋፍ ለደረሰው ስርዓት ግዜ በማስገኘት ለማሰንበት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊነትን ማወደስም ቢሆን የህዝቦችን ጥያቄ ኣቅጣጫውን በማሳት ምላሽ እንዳያገኝ በማድረጉ ላይ ያተኮረው እንደማደናገሪያ ሊገለገልበት እንጂ ምላሽ ሊሆን እንደማይችል ከኦፒዲኦ/ኢህኣዴግ ግንዛቤ ውጪ ኣይደለም። ይህ ደግሞ የፖለቲካ ችግርን ከመፍታት በመሸሽ በቀጣይነት ለሚካሄድ ጦርነትና ግጭት ከተጠያቂነት እንዲወጡ ኣያደርጋቸውም።

ከወያኔ/ኢህኣዴግ መንግስት መዳከም የተነሳ ዛሬ ትላንት ማንነታቸውና ዓላማቸው በመታወቁ ህዝቦች ከጫንቃቸው ላይ ያወረዷቸው፣ ተመልሰው ነፍስ በመዝራት ፍትሃዊውን የህዝቦች ትግል ሲያወግዙና ሲኮንኑ እየታየ ነው። ህዝቦች በቋንቋቸው መማር፣ በማንነታቸው ተደራጅተው ለመብታቸው መፋለም፣ ለቋንቋቸው ፊደል ከማውጣቱ ጥላቻ ያደረባቸው፣ ይህ ፊደል “የሰይጣን ነው” በማለት ሲያወግዙ የነበሩ ዛሬ ደግሞ የህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት “የሰይጣን ሃሳብ ነው” በማለት በይፋ የነጻነት ታጋይ ህዝቦችን እያጣጣሉን እየተሳደቡ ነው። ሃይማኖትን ከለላ በማድረግ በህዝቦች ላይ እየዘመቱ ያሉት እነዚህ ጸረ፥ ነጻነትና ዲሞክራሲ ሃይሎች ፍትሃዊ ጎዳና ብለው የሚለፍፉት በሃይል በህዝቦች ላይ የሚጫን ኣንድነት፣ የኣንድን ብሄር የበላይነት በሌሎች ህዝቦች ላይ መጫን መሆኑ ከተጨቋኝ ህዝቦች ግንዛቤ ውጪ ኣይደለም።

የኢትዮጵያን ኢምፓየር ለዓመታት ኣንቆ ለያዘው ፖለቲካ ዘላቂ መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ የትላንቱን ስርዓት ለመመለስ የሚያዛጉትም ሆኑ ኣሁን ስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ለማስቀጠል እየተወራጩ ያሉት የትግሉ ኣካል ሳይሆኑ የችግሩ ኣካላት ናቸው። ዛሬ ወያኔ/ኢሕኣዴግ ላለፉት 27 ዓመታት በህዝቦች ላይ ለፈጸመው ወደር-የለሽ ክፋት መጠየቅ ሲገባው የተወለደበትን ዕለት ግንቦት 20ን ህዝቦች በብዛት ወጥተው እንዲያከብሩ እየጠየቀ ነው።

የወያኔ/ኢህኣዴግ በዓል የህዝቦች በዓል ነው በሚል እንዲከበር ኣቤቱታ ቢያቀርብም ይህ ቀን የፋሽስቶችና የኣሸባሪዎች ቡድን ኣሁን የያዘውን ስልጣን በሃይል የተቆጣጠረበት ዕለት ነው ። ላለፉት 27 ዓመታት በቆየበት ዘመነ-ስልጣንም በኦሮሞ ህዝብ ላይ ታይቶም-ተሰምቶም የማይታወቅ ወንጀል ፈጽሟል።

 * የኦሮሞ ህዝብ ከወተር ኣንስቶ እስከ ሞየሌ ድረስ በጅምላ መገደሉ

*  የኦሮሞ ህዝብ መብቱ እንዲከበር በመጠየቁ ብቻ “ሁሉም የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ኣፋን ኦሮሞ ይናገራሉ” እስከሚባል ድረስ በጅምላ ወደ ወህኒ መጋዙ

*  ለሁለት ጊዜያት በታወጀበት የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ሃብቱ እየተዘረፈ፣ ወደ እስር ቤት ኣየተጋዘና እየተገደለ ያለመሆኑ፥ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ ከመታወጁም ውጪ ለ27 ዓመታት ጦር ሃይል ሰፍሮበት የተለያዩ የጦርነት ዘመቻዎችን ሲያካሄድበት እንደነበር

 እራሳቸው ለመ ክበር ሲሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ዜጎችን ከትውልድ ቀዬኣቸው በማባረር ለረሃብና ድህነት ማጋለጡ

*  በኢንቨስትመንት ስም በኦሮሚያ ሃብት ላይ ኣይን ያወጣ ዝርፊያ በመፈጸም ራሳቸውን ማድለብ በሚኖርበትና በሃገሩ ውስጥ በማስወረርና በመውረር ማፈናቀል

 * ወደ ጦር ካምፕ በተቀየሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ “ኮማንድ ፖስት” በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንዳለ፡ ተዘርዝሮ የማ ያልቅ ቁጥር-ስፍር የሌለው ዘግናኝ ድርጊት መፈጸሙ እየታወቀ ስልጣን የያዝኩበትን ዕለት ኣክብሩልኝ ማለቱ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።

የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ወያኔን አጥብቆ ያውቃል። ወያኔ/ኢህኣዴግ መቼም ለኦሮሞ ህዝብ ዘመድና አጋር ሆኖ ኣያውቅም። ቀዳሚ ጠላቱ ኣድርጎ ባወጀበት ዘመቻ በጅምላ እየረሸነና በቀዬው ውስጥ ወንድ-ሴት፣ ህጻን-ጎልማሳ፣ ሽማግሌ-ኣሮጊት ሳይል ሲገድል የነበረና እየገደለም ያለ የፋሽስቶች ጥርቅም ነው። ከግድያም ባሻገር የኦሮሞ ዜጋ ኣስክሬን ቀብር ተነፍጎ የኣሞራና የኣውሬ እራት እንዲሆን ያደረገ፣ በኣውሬነት ከፍተኛና ዘግናኝ ወንጀል የፈጸመ ቡድን ነው። የኦሮሞ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት የተፈጸመበትን ጭካኔ በጣልያን የኣገዛዝ ዘመንም ያላየው ነው። ስለሆነም ግንቦት 20 ጸረ ህዝብ ሃይሎች ወደ ስልጣን በመውጣት ኑሮውን ያጨለሙበት ስለሆነ ላለፉት 27 ዓመታት ከስርዓቱ ጀሌዎች በስተቀር ህዝቡ እንደ በዓል ኣክብሮት ኣያውቅም፥ ማክበርም አይጠበቅበትም።

ለውጥ ተብሎ በሃሰት በሚለፈፈው ባሁኑ ወቅት የወያኔ/ኢህኣዴግ ወኪል በመሆን የስርዓቱን እስትንፋስ ለማቆየት ቃል የገቡትም በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየተካሄደ ያለውን ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ዝርፊያና የስነ-ልቦና ዘመቻ ማስቆም ኣልቻሉም። የህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ከሚቃወሙት ጋር በማበር ጸረ-ህዝብነታቸውን እያሳዩ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ትግል ዛሬ ካሉበት ደረጃ ያደረሳቸው፡ በህዝቡ ላይ የሚፈጸመ ውን ክፋት ከማስቆምይልቅ በየመንደሩ እየተዘዋወሩ የጠላትን ዓላማ እንዲቀበል ለማድረግ መሯሯጥን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።

ከዚህም ውጪ ከነሱ የሚጠበቅ ስለሌለ በኣዲስ ተብዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ስም የኦሮሞ ህዝብ ቀዬ ሰላም ኣላገኘም። ግድያና እስራት እንደቀጠለ ነው። ዝርፊያ ተስፋፍቷል። ከዚህም ኣልፎ የኦሮሞ ህዝብ እያቀረበ ያለውና በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች መስዋዕት የሆኑበትን የሃገር ባለቤትነት መብት ጥያቄ “የሰይጣን ስራ ነው” በሚል ሲወገዝ በመንግስት ሚድያና፣ ደጋፊዎቻቸው እንዲራገብ እየተደረገ ነው። እነሱም ወደ ኦፒዲኦ በመጨመር ኦሮሙማ ማለትንና ለኦሮሚያ ከመፋለም ተቆጠቡ፥ ኣውግዙ እያሉ ነው ። እንግዲህ ይህ መንግስት ነው ግንቦት 20ን ህዝቦች በነቂስ ወጥተው እንዲያከብሩለት እየተማ ጸነ ያለው።

የኦሮሞ ህዝብ ጠላቶቹና ባልንጣዎቹ እንደሚያዩት ኣይደለም። ወዳጁንና ጠላቱን ለይቶ ያውቃል። ስለሆነም በ27 ዓመታት የወያኔ የመከራ ኣገዛዝ ዘመን ውስጥ ግንቦት 20ን የኔ ብሎ በመቀበል ያከበረበት ቀን የለም። የኦሮሞ ህዝብ ይህ ቀን ከጠላት የፈረጁት ጨቋኞችና ዘራፊዎች በጫንቃው ላይ ስልጣናቸውን ያደላደሉበት ዕለት መሆኑን ነው የሚያውቀው። ይህ ቀን የኦሮሞን ህዝብ ደመ ኛ ጠላቱ ያደረገው ቡድን ስልጣን የተቆናጠጠበት ዕለት መሆኑን ይገነዘባል። ስለሆነም ግንቦት 20 በምንም መልኩ የኦሮሞን ህዝብ ኣይመለከትም። በገዢዎች እንዲከበር የሚፈለገው ማንኛውም ዕለት የህዝቦችን ጥቅም የማያስከብር ጸረ-ነጻነት ዲሞክራሲና ጽረ-ሰብዓዊ መብት ስለሆነ የኦሮሞ ህዝብ ለወያኔ ጀሌ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ኣይሰጥም።

ዘመኑ የጭቆና ፍጻሜ ዘመን ነው!

ድል ለኦሮሞ ህዝብ!

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር

ግንቦት 22, 2018ዓም