የኦሮሞ ጀግኖችና ሚያዚያ 15, የኦነግ መግለጫ

ሁሉም ሃገራትና ህዝቦች በታሪካቸው ውስጥ ለህዝባቸውና ለሃገራቸው ታላቅ ስራ በመስራት የሚዘከሩ ጀግኖች ኣሏቸው። ጀግንነት ሃይል፣ ሃብት፣ እውቀትንና ህይወትንም ጨምሮ ከግል ጥቅም በይበልጥ ለህዝብ ወይንም ለሃገር ጥቅም በማዋል የሃገርና የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ መቻል ነው። በማንኛውም ሃገር ኣልያም ህዝብ ውስጥ የሃገርና የህዝብን ህልውና ኣሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚጥል ኣደጋ ወይንም ችግር ኣልያም ደግሞ የባዕድ ወረራ ሲያጋጥም በግንባር ቀደምትነት ተሰልፎ ሃገርና ህዝብን ከኣደጋ ለመጠበቅ መስዋዕትነት የሚከፍል ጀግና ነው። ስለሆነም ጀግና የሃገርና የህዝብ ኣለኝታ ነው። ጀግኖች ለሃገራቸውና ለህዝባቸው ሞገስና ጋሻ ናቸው። በመሆኑም ሁሉም ህዝቦችና ሃገራት ለጀግኖቻቸው ታላቅ ክብር ይቸራሉ። የጀግኖች ቀን በማለትም በየኣመቱ ይዘክሯቸዋል።

በህዝባችን ታሪክ ውስጥም ህዝቡ በሃገሩ ላይ ነጻነቱና ሉዓላዊነቱ ተጠብቆ በሰላም፣ በብልጽግናና በክብር እንዲኖር ለማስቻል ከባዕዳን ወረራ ለመከላከል በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው ህይወታቸውን የሰዉ የኦሮሞ ጀግኖች እልፍ-ኣእላፍ ናቸው። የሩቁን ትተን ከቅርቡ ብንጀምር እንኳ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ኣጋማሽ የኣጼ ቴዎድሮስ ዘመቻ በሰሜን በኩል በኦሮሞ ላይ ከተከፈተበት ጊዜ ኣንስቶ ኦሮሞ በኣውሮፓውያን እገዛና በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ተበልጦ በመሸነፍ በባዕዳን የኣገዛዝ ስርዓት ስር ለመውደቅ እስከተዳረገበት ድረስ ነጻነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ በጀግንነት ሲዋጉ የተሰዉት የኦሮሞ ጀግኖች በሺዎች ሳይሆን በሚሊዮን እንደሚቆጠሩ ታሪክ ይመሰክራል።

ለባዕዳን የኣገዛዝ ስርዓት ወይንም ቅኝ-ኣገዛዝ ከተዳረገ በኋላም ህዝባችን የባርነት ኑሮን ተቀብሎ ኣሜን ብሎ ተኝቶ ኣላደረም። በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ባመቸው ሁኔታ ሁሉ ተጠቅሞ በሃይል ሃገሩን ወርሮ የያዘውን ባዕድ ከላዩ ላይ ለማንሳት ያልተቋረጠ ጥረት ሲያደርግ ነበር። በዚህ መልኩ በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት የኦሮሞ ጀግኖች የባዕዳንን ኣገዛዝ በመቃወም ካደረጓቸው ጥረቶች መካከል የራያ፣ የዳዌና የባሌ እንዲሁም የመጫና ቱለማ ንቅናቄ የጀግንነቱ ማሳያዎች ናቸው።

የኦሮሞ ህዝብ ነጻነቱንና ሉዓላዊነቱ መልሶ ለመጎናጸፍ በተለያየ መልኩ ሲያካሄ ከነበረው ንቅናቄ የተወለደው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከተመሰረተበት ጊዜ ኣንስቶ ቆራጥ ብሄርተኞች፣ ምሁራንና ጀግኖች የኦሮሞ ልጆች በግንባሩ ስር በመሰለፍ ለኦሮሞ ነጻነትና ለኦሮሚያ ሉዓላዊነት ከባድ መስዋዕትነትን ሲከፍሉ ዛሬን ደርሰዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ውድ ጀግኖች ልጆች ለነጻነት የከፈሉትን ይህን መስዋዕትነት እንደህዝብ ተገቢውን እውቅናና ክብር ሰጥቶ በየዓመቱ እንዲዘክር በ1984ዓም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሚያዚያ 15: የኦሮሞ ጀግኖች/ሰማዕታት ቀን በማለት ኣወጀ። ከዚያን ወቅት ኣንስቶ ሚያዚያ 15 የኦሮሞ ጀግኖች ቀን መሆኑ ታውቆ በየዓመቱ በግንባሩ ኣባላትና ደጋፊዎች ተከብሮና ተዘክሮ መዋል ጀመረ። ቀስ በቀስም የመላው የኦሮሞ ህዝብ የሚዘክረው ቀን ሆነ።

ሚያዚያ 15 የኦሮሞ ጀግኖች ቀን እንዲሆን የተመረጠው ኣጥጋቢና ታሪካዊ ምክንያት ኣለው። ሚያዚያ 15 ቀን 1980ዓም የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን በመመስረቱና በመምራት እንዲሁም የትጥቅ ትግል ሜዳን በመክፈትና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በማቋቋሙ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው የኦሮሞ ጀግኖች(የወቅቱ የኦነግ ሊቀ-መንበርና ምክትሉ) እንዲሁም የጦር መኮንኖችና ነባር ካድሬዎች የሚገኙበት 10 ሰዎች ለታላቅ የትግል እንቅስቃሴ ተልዕኮ በጉዞ ላይ ሳሉ በኣንድ ቦታ ኣብረው በመሰዋት በኣንድ ጉድጓድ ተቀበሩ። ይህም የሆነው እነዚህ ጀግኖች የኦሮሞን ህዝብ ኣንድነት ከፍተኛ ፈተና ላይ ሊጥል የሚችል ከባድና ዘግናኝ ኣደጋ ባጋጠማቸው ጊዜ የኦሮሞን ኣንድነት በማስቀደም ላለመለያየት በመወሰን ኣብረው መሰዋትን መምረጣቸው ነው። በዚህም ከትውልድ ኣካባቢ፣ ከጎሳና ከሃይማኖት በበለጠ የሚያሰባስበን የኦሮሞነት ኣንድነታችን መሆኑን ኣስተምህሮት የሚሰጥ የኣንድነታችንን ሃውልት በደምና በኣጥንታቸው ለተተኪው ትውልድ ተክለው ኣለፉ። ይህም የሆነው ዛሬ የሶማሌ ክልል ተብሎ በሚጠራው ክልል ውስጥ በምትገኘዋ ሽኒገ በተባለች ቦታ ነው።

በዚህ መልኩ የጀመረው የኦሮሞ ጀግኖች ቀን ታሪክ በኣሁኑ ወቅት በመላው የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ (በሃገር ቤትና በውጪም) ኦሮሞ ነጻነቱንና የሃገር ባለቤትነት መብቱን ለማስከበር የተሰዉትን ሁሉንም ጀግኖች ልጆቹን ዘክሮ የሚውልበት ቀን ሆኗል። በመሆኑም በዚህ ቀን(ሚያዚያ 15) ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር የተለያዩ መስዋዕትነቶች የከፈሉትን ሁሉንም የኦሮሞ ጀግኖች እንዘክራለን። ጀግኖቹን ኣስበን መዋል ብቻም ሳይሆን ጀግኖቻችን የተሰዉለትን ዓላማ(ኦሮሞ በኦሮሚያ ላይ ሊኖረው የሚገባውን ነጻነትና የሃገር ባለቤትነት መብት) ከግቡ ለማድረስ ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ነው።

ዛሬ የ2018ቱን የኦሮሞ ጀግኖች ቀን(ሚያዚያ 15 ቀን 2018ዓም) ስናከብር ጀግኖቻችን ተሰዉተውለት ከዛሬ ያደረሱትና ዛሬም መስዋዕትነት እየከፈሉለት ላለው የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ካለበት ሁኔታ ጋር ኣያይዘን ከዚህ በታች ያሉትን ጉዳዮች ማስታወስ ኣስፍላጊ ይሆናል፡

  • ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ(የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል) በዓለም ማህበረሰብ ፊት በግልጽ ተሰሚነት ማግኘትጀምሯል። የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ኣገዛዝ ስርዓቶች ያለው ጥያቄ በባዕዳን ዘንድ ግልጽ ሆኗል። ኦሮሞ ከምስራቅ-ምዕራብ፣ ከሰሜን-ደቡብ፣ ከውስጥና ከውጪ ሃገራት በመደማመጥና በመግባባት በኣንድነት የነጻነት ጥያቄን በማስተጋባት ላይ ነው። በተለይም የቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ንቅናቄ በኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግልና ከመላው ኢምፓዬሪቷም ኣልፍ ለሌሎችም የዓለም ተጨቋኝ ህዝቦች ተምሳሌት እየሆነ ነው። በዚህም ጸረ-ዲሞክራሲና ጸረ-ህዝቦች የሆነው የኢትዮጵያ ኢምፓዬር የጭቆና ኣገዛዝ ስርኣት ከመሰረቱ ተናግቷል።
  • የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ ሊደርስ የቻለው የጀግኖቻችን ደም ለዓመታት ፈስሶ፣ ጥንታቸው ተከስክሶ፣ መተኪያ የሌለው ህይወታቸው በእልፍ-ኣእላፍ ተሰውቶበት ነው። ይሁን እንጂ ትግሉም ሆነ ለትግሉ የሚከፈል መስዋዕትነት ዛሬም እንደቀጠለ ነው። የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰውን ይህን ትግል በከፍተኛ ቆራጥነትና ንቃት ይበልጥ በማፋፋም ከግቡ በማድረስ ለጀግኖቻችን መስዋዕትነት ፍሬ ማስገኘትና በነጻነት ካስ መንቀሳቀስ የሁሉም የኦሮሞ ብሄርተኞችና ታጋዮች ግዴታ መሆኑን ኣጥብቀን መገንዘብ ይጠበቅብናል።
  • ዛሬ በኢሕኣዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡን ሊያሞኝበት የሚሻውን የሃሰትና የማስመሰያ ለውጥና ፍትሃዊውን የኦሮሞ የነጻነት ትግል እውነተኛ ዓላማ ለማጥላላትና ኣጣምሞ ለማቅረብ “በኢትዮጵያዊነት” ስም በስፋት እየነዛ ያለውን ፕሮፓጋንዳ በከፍተኛ ንቃት ታግለን በማሸነፍ ለጀግኖቻችን መስዋዕትነት ፍሬ ማስገኘት ወሳኝ ጉዳይ ነው።
  • ከሁሉም በላይ የኦሮሞ ህዝብ ለነጻነቱ ያነሳውና ለዘመናት ከባድ መስዋዕትነት እየከፈለበት ያለውን ፍትሃዊ ጥያቄ በኣፋቸው ትክክል ነው እያሉና ለኦሮሞ የሚቆረቆሩ መስለው፡ በተግባር ግን የኦሮሞ ህዝብ ፍትሃዊ ትግል ከግቡ እንዳይደርስ ለማድረግ ኣልያም ካለመለት ግብ ለማስቀየር ከጠላት ጋር ኣብረው በኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ላይ ተንኮል የሚሸርቡትን በንቃት በመጠበቅ ይህን እኩይ ዓላማቸውን ማምከን ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው።
  • የኦሮሞ ህዝብ ባጠቃላይ፣ በተለይም ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ የነጻነት ትግሉና የቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ኣካል መስለው ቄሮን ለማጥፋት እየሰሩ ያሉትን ግለሰቦችና ቡድኖችን በንቃት በመጠበቅ የኦሮሞን ህዝብ የነጻነት ትግል ጎራ ከጠላት ሴራ የጸዳና የተረጋጋ ለማድረግ መንቀሳቀስ የግድ ይላል።

በመጨረሻም ጀግኖቻችን የተሰዉለት ዓላማና ግብ የኦሮሞ ህዝብ እንደህዝብ ሊኖረው የሚገባውን ነጻነትና ሉዓላዊነት በትግሉ እንዲጎናጸፍ ማስቻል ነው። ህዝባችን ይህን እንደህዝብ ያለውን ከሁሉም የላቀ መብቱን በእጁ እስካላስገባ ከኣንድ ምዕተ-ዓመት ተኩል በላይ ከተጫነበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮችና ጭቆና ለመላቀቅ ዋስትና ኣይኖረውም። ስለሆነም በኦሮሞ ህዝብ የነጻነትና የሃገር ባለቤትነት መብት ጥያቄ የሚያምኑ የኦሮሞ ልጆች ሁሉ የኦሮሞን የነጻነት ትግል ከግቡ በማድረስ የጀግኖቻችንን መስዋዕትነት ዋጋ በነጻነት ለመካስ በያለንበት የነጻነት ትግሉን እንድናፋፍም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መልዕክቱን ያስተላልፋል።

ድል ለኦሮሞ ህዝብ !
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ሚያዚያ 13 ቀን 2018ዓም