ችግራችን ተፈትቶ የተነፈግነው ፍትህ የሚረጋገጠው ነጻነታችንን ተቀዳጅተን የሚበጀንን መንግስት ስንመሰርት ብቻ ነው

ችግራችን ተፈትቶ የተነፈግነው ፍትህ የሚረጋገጠው ነጻነታችንን ተቀዳጅተን የሚበጀንን መንግስት ስንመሰርት ብቻ ነው

(የኦነግ መግለጫ – ሓምሌ 16, 2018ዓም)

addaከሶስት ወራት በፊት ዶር. ኣብይ ኣህመድ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሾመ ወዲህ ብቻ በሶማሌ ‘ልዩ ሃይል’ በኦሮሞ ህዝብ ላይ በተካሄደ ጦርነት ብቻ በምስራቅ፣ በደቡብ-ምስራቅና በደቡብ ኦሮሚያ በኩል ከ535 በላይ የኦሮሞ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል። ከነዚህም ውስጥ 185 ሰዎች ባለፈው ኣንድ ወር ውስጥ ብቻ የተገደሉ ናቸው። እነሱም፡ በጭናክሰን 43፣ በባቢሌ 17፣ በሚኤሶ 23, በጉርሱም 11, በመደ-ወላቡ 13 እና በጉጂና በቦረና 78 ሰዎች መሆናቸው ተረጋግጧል። ይህ መረጃ የተሟላ ነው ማለትም ኣስቸጋሪ ነው። በነዚህ ውጊያዎች ውስጥ ከ600 በላይ የሚሆኑ የህዝቡ መኖሪያ ቤቶች በእሳት ጋይተው እንስሳትም በቁማቸው ከቤቶች ጋር ተቃጥለዋል። በብዙ ሚሊዮኖች ገንዘብ የሚገመት የህዝብ ሃብትም በዚህ ኣጭር ጊዜ ውስጥ በውጊያው ወድሟል።

ይህ ጦርነት ኣሁን ኣዲስ የተጀመረ ሳይሆን ለበርካታ ዓመታት በምስራቅ፣ በደቡብ-ምስራቅና በደቡብ በኩል በዚሁ ‘የሶማሌ ልዩ ሃይል’ በተባለ ሃይል በኦሮሞና በኦሮሚያ ላይ ሲካሄድ የነበረ ጦርነት ኣካል ነው። ይህንን ጉዳይ ኣስመልክቶ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በተደጋጋሚ የተለያዩ መግለጫዎችን ሲያወጣ ቆይቷል። በመግለጫዎቹ ውስጥም ይህ ጦርነት እያስከተለ ያለውንና ለወደፊቱም ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገቧቸውን እርምጃዎች ሁሉንም የሚመለከታቸውን ኣካላት ሲያስገነዝብ ነበር። ከነዝህም መካከል “የሰላማዊ(መሳሪያ-ኣልባ) ህዝብ ህይወትና ንብረት ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል” በሚል ርዕስ ስር መስከረም 15 ቀን 2018ዓም ኦነግ ያወጣው መግለጫ ኣንዱ ነው። ቁ. 013/stm-abo/2017

እንደክብደቱ ሲታይ ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ኢምፓዬር እየታዩ ካሉት የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች መካከል ቅድሚያ ተሰጥቶት ኣጥጋቢ ምላሽ ማግኘት የሚገባው መሆኑን ኦነግ በጽኑ ያምናል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር. ኣብይ ኣህመድ የዚህን ጦርነት ጉዳይ እንደስጋት ኣንስተው ለመናገር እንኳ እስከ ሃምሌ 14 ቀን 2018ዓም ድረስ (ተሹመው ከ3 ወራት በላይ) ጊዜ ወሰደባቸው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተባለው ኣካልና ኦፒዲኦም ይህንን ጦርነት ከኦሮሞ ህዝብ ላይ ከመመከት ይልቅ ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና ከቄሮ ባላቸው ጥላቻና እልህ ተሞልተው ኣሁን እየታየ ያለውን ለውጥ ለማስገኘት በግንባር-ቀደምትነት ታግለው ውድ መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩትንና ኣሁንም በመክፈል ላይ ያሉትን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞን በማደን ላይ ጊዜያቸውን፣ ሃብታቸውንና ሃይላቸውን በማባከን ላይ ይገኛሉ።

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው የህዝባችን ህይወትና ንብረት በዚህ ደረጃ እየወደመ ባለበት በዚህ ወቅት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ኦፒዲኦ ለዚህ ጉዳይ ደንታ በማጣት የኦነግን ስም ያጠቁርልናል ያሉትን ርካሽ ፕሮፓጋንዳ በማራገብ ላይ መሰማራታቸው ነው። “በኦሮሚያ ምክር ቤት/ጨፌ ኦሮሚያ” ላይ ሳይቀር ለዚህ የህዝብን ህይወትና ሃብት እያጠፋ ላለው ከባድ ጉዳይ በቂ ትኩረት ባለመስጠት የፖለቲካ ጥቅም ያስገኝልናል ብለው ላሰቡት በሃሰት የተሞላ ፕሮፓጋንዳና የስም ማጣፋት ዘመቻ ቦታ መስጠታቸው ለዚህ እውነታ ኣብይ ምስክር ነው። ይህ ችግርም የኦሮሞ ህዝብ እሱን የሚያደማ፣ ሃብቱን የሚዘርፍና የሚያስዘርፍ፣ ከመሬቱ የሚያፈናቅለው እንዲሁም የሚገድለውና የሚያስገድለው መንግስት እንጂ ለሱ የሚደማ፣ ለሱ የሚሰራና የሚራራለት እንዲሁም በችግር ጊዜ የሚደርስለት መንግስት ከማጣቱ ብቻ ይመነጫል።

ለበርካታ ጊዜያት ደጋግመን እንደገለጽነው ይህን የሶማሌ ልዩ ሃይል ሆን ብሎ ኣሰልጥኖ ኣደራጅቶ በማስታጠቅ በኦሮሞ ላይ ያሰማሩት በኢህኣዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የሕወሃት ጄኔራሎች ናቸው። ዛሬም ቢሆን የኢህኣዴግ ኣባላት በስልጣን ወንበር ላይ ተቀያየሩ እንጂ በኢህኣዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ስርዓት ከመሰረቱ ኣልተቀየረም። እነዚህ የሕወሃት ጄኔራሎች እንዲህ ባለው ዘግናኝ ግድያ ላይ ሲሰማሩ በዝምታ ማየት ከመሰረቱ የተቀየረ ነገር ኣለመኖሩን ግልጽ ያደርጋል።

ስለሆነም የህዝቦች ችግር መሰረት የሆነው በጠመንጃ ኣፈሙዝ ተቋቁሞ ሲጠበቅ ዛሬን የደረሰው የኢትዮጵያ ኢምፓዬር የፖለቲካ ስርዓት ከስር-መሰረቱ ተቀይሮ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ሌሎች ህዝቦች ሙሉ ነጻነት ተጎናጽፈው ያለኣንዳች ጫና በነጻነት የሚበጃቸውን መንግስት ከውስጣቸው መርጠው ሊተዳደሩበት የሚችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ህይ ችግር ኣይገታም። በተለይም ደግሞ በሕወሃት ከፍተኛ የፖለቲካ ሹማምንትና የጦር መኮንኖች(ጄኔራሎች) ታቅዶ በሶማሌ ልዩ ሃይል በኦሮሞ ላይ ሲካሄድ የነበረውና እየተካሄደም ያለው ጦርነት የኢህኣዴግ ስርዓት ከመሰረቱ እስካልተነቀለ ድረስ ሊቆም የማይችል መሆኑን ማስገንዘብ እንሻለን።

ስለሆነም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ፣ በሃገር ቤትና በውጪ ሃገራት የሚገኙ የኦነግ ኣባላትና ደጋፊዎች ሁሉ እንዲሁም መላው የኦሮሞ ብሄረተኞች (በመንግስት መዋቅርና በተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ) ህዝባችን ያለበት ህይ ችግር ነጻነቱንና ለሱ የሚሆነውን (የሚደማለትና የሚራራለት) መንግስት ከማጣት የመነጨ መሆኑን ተገንዝበን ለመፍትሄው የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ ኦነግ መልእክቱን ያስተላልፋል። ስለሆነም ወታደራዊ ስልጠና ያላችሁ በኣካል/በሞያችሁ፣ ሌሎች ደግሞ በገንዘብና ቁሳቁስ ለከፋ ጉዳት እየተዳረገ ካለው ህዝባችን ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናድሳለን። ይህ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ኣካባቢ ኣቅራቢያ የምትገኙ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ኣባላት ይህንን ጦርነት ከህዝባችን ላይ በመመከቱ ላይ ግዴታችሁን እንድትወጡ እያሳወቅን፡ በሩቅ ያላችሁትም ለህዝባችን በመድረስ ኣብራችሁት እንድትቆሙ እናሳስባለን።

መላው ማህበረሰባችን ይህ ችግር ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መሰረታዊ ችግር መሆኑን ይበልጥ ተረድተን ለዚህ የህዝባችን ችግር የመጨረሻና ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት ከያለንበት ሁሉ የህዝባችንን የነጻነት ትግል በተቻለልን ሁሉ እንድናፋፍም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣጥብቆ ጥሪውን ያቀርባል። ችግራችን ተፈትቶ የተነፈግነው ፍትህም የሚታየው ነጻነታችንን ተጎናጽፈን የሚበጀንን መንግስት ስናቋቁም ብቻ ነው። በኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሚመራው የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግልም ግቡ ይህንኑ ማረጋገጥ ነው።

ዘመኑ የጭቆና ፍጻሜ ዘመን ነው !
ድል ለኦሮሞ ህዝብ !

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ሃምሌ 16, 2018ዓም