ንጹሃን ዜጎችን በመግደል የሚረጋገጥ ድል የለም በንጹሃን ዜጎች ግድያ ላይ የተሰጠ የኦነግ መግለጫ

ንጹሃን ዜጎችን በመግደል የሚረጋገጥ ድል የለም
በንጹሃን ዜጎች ግድያ ላይ የተሰጠ የኦነግ መግለጫ

መስከረም 26/2022
በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በሚካሄደው ጦርነትና በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው አሳዛኝ ሰቆቃ አለም አዉቆት እያወግዘዉ ባለበት በዚህ
ጊዜ በኦሮሚያ ዉስጥ ያለው ጭፍጨፋ ግን ሆን ተብሎ እንዳይሰማ ተደርጓል፡፡ የአለማቀፉ ማህበረሰብም በጉዳዩ ላይ ዝምታን
መርጧል፡፡ በመንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ስፋት እየተፋፋመ ይገኛል፡
፡ የ ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ይዞታዎቹን ከገጠር ወደ ወረዳ እና ዞኖችን ጨምሮ ወደ ትላልቅ ከተሞች እያስፋፋ ይመስላል።
የታጠቁትን የነጻነት ሃይሎች እናጠፋለን በሚል ሰበብ የመንግስት ሀይሎች፤ የአማራ ፋኖ ፤ የአማራ ክልል ሚሊሻ እና ልዩ ሃይሎች
የምዕራብ ኦሮሚያን በተለይም ሆሮ ጉዱሩን እና ምስራቅ ወለጋን ወረዋል፡፡
ከአሁን በፊት የፌደራል ሃይሎች እና የአማራ ፋኖ አጋምሳ ዉስጥ በነሃሴ 30, 2022 ከ63 በላይ ንጹሃን መግደላቸውን እንዲሁም
በአቡና እና ጉዲና አቡና በመስከረም 3, 2022 የፌዴራል ሀይሎች፤ የአማራ ፋኖ እና የአማራ ከልል ልዩ ሃይል በፌደራል ሃይል
በመታገዝ 31 ንጹሃን ሰዎችን ማረዳቸዉን በሚመለከት የሰጠነዉን መግለጫ ማየት ይቻላል፡፡
ጉዳዩን ይበልጥ ለማወሳሰብ የአማራ ክልል ሃይሎች እና ፋኖ ከመስከረም 22, 2022 እስከ መስከረም 26, 2022 የኦሮሚያን ድንበር
ጥሶ በመግባት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት የግፍ ጭፍጨፋ እና ግድያ ፈጽመዋል፡፡ ባደረጉት የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ
በጃርዳጋ ጃርቴ እና አሙሩ ወረዳዎች በተለይም ቅልጡ ጨካ፤ ሃሮ ዋሎ ቶምቤ፤ዳንጋብ፤ሃሮ ጉዲና እና ዳርጌ ኮቲቻ በተባሉ ቀበሌዎች
ዉስጥ ባጠቃላይ ከ100 በላይ ንጹሃን ዜጎችን በጭካኔ ገድለዋል፡፡ እንዲሁም በአሙሩ ወረዳ በተለይም አጋምሳ ከተማ፤ ሚጊር፤ ሳሞ፤
ዋስቲ፤ ሉማ’እ፤ ጃዋጃ፤ ጃቦ ዶባን፤ ጭዳቲ፤ ጎቡ፤ ኛሬ፤ ማካኖ፤ ሾኬ እና ዳምጋብ ሲዳን በተባሉት ቦታዎች ተመሳሳይ የጭካኔ ግድያዎች
ተፈጽመዋል፡፡ በኪራሙ ወረዳ ሃሮ ቀበሌ እንዲሁ ንጹሃን በጭካኔ ተገለዋል፡፡ በሺዎች በሚቆጠሩ የታጠቁ ማህበረሰብ ፉከራ እና
ሽለላ ተደግፎ እየወረረ ያለዉ የአማራ ልዩ ሃይል በፌደራል ሃይሎች እና በአማራ ሚሊሻ በሚደረግለት ድጋፍ እና አመቻችነት መሆኑ
ግልጽ ነው፡፡ የፌደራል ሃይሎች፤ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ፋኖ ሆነዉ በተቀናጀ ሁኔታ እናቶች፤ ሀጻናት እና አዛዉንቶችን
ሳይቀር ያለ ርህራሄ መጨፍጨፋቸዉን የአካባቢ ነዋሪዎች እና ከግድያው የተረፉት ሰላማዊ ሰዎች መስክረዋል፡፡ አንድን ብሄር
በተለይ ኦሮሞን ከቄው ላይ ለማጽዳት ኢላማ ያደረገ ግድያ እና ጭፍጨፋ የዘር ማጥፋት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት የከሸፈ ቢሆንም ገዥው ቡድን አንዱን ከሌላዉ በማጋጨት እያደረገ ያለዉ ሙከራ እየተሳካለት ይገኛል፡፡ የዚህን
አስከፊ ዉጤት መገመት ግን እጅጉን አዳጋች ይሆናል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብን እና
የአለማቀፉን ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
ይህ ማለቂያ የሌለዉ የንጹሃን ዜጎች እልቂት አሁን እጅጉን አስጊ እና መጥፎ ደረጃ ላይ መድረሱን በድጋሚ እናሳስባለን፡፡ የመንግስት
በግድ የለሸነት የተሞላ ወታደራዊ ዘመቻ የታሰበዉን ያክል ውጤት አያመጣም፡፡ ይልቁን የንጹሃንን ሞት ያባብሳል፤ የንብረት ዉድመትን
እና ሰብኣዊ ሰቆቃን በመጨመር ነገሮችን ወዳልተፈለገ ያመራል፡፡ እድሜያቸዉ ያልደረሰ ህጻናትን ከትምህርት ቤት በጉልበት አጉሮ
ለወታደራዊ ስልጠና መመልመል የወንጀል ድርጊት ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ መመርያ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የወታደራዊ
አማራጭ ለግጭቶቹ መፍትሄ እንደማያመጣ ቢታወቅም በተከታታይ ኢትዮጵያን የመሩት ገዥዎች ግን እንደ ባህል ሆኖባቸው ይህንኑ
መንገድ አማራጭ በማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡ ሊታወቅ የሚገባዉ ጉዳይ ግን ገዥዉ ቡድን የብዙ መቶ ሽዎቸን ዜጎቸ ህይወት ከቀጠፈ
በዉሃላ መሽነፍ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አያዳግትም፡፡
የኦሮሞ ህዝብ በተለይም የጥቃት ኢላማ የተደረጉት የሆሮ ጉዱሩ እና ምስራ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ምንም አማራጭ ስሌለላችሁ
ልጆቻችሁን እና ንብረታችሁን እንድትታደጉ ኦነግ በድጋሚ ያሳስባል፡፡ መንግስት በእብሪተኝነት የራሱን ህገመንግስት እና የአለማቀፉን
ህግ በቋሚነት ጥሷል፡፡ እራሳችሁን በመከላክል በምታደርጉበት እንቅስቃሴ የሚመለከታቸሁ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ያልታጠቁ
ሰላማዊ ዜጎችን እና ንብረታቸዉን ያለምንም መድሎ ማለትም ሃይማኖት እና ብሄርን ሳይለዩ ጥበቃ እንዲያደርጉላቸዉ ኦነግ ጥሪ
ያደርጋል፡፡ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ከለላ ሊደረግላቸዉ ይገባል፥ ደህንነታቸዉንም ማረጋግጥ ግድ ይላል፡፡