በታጋይ እና አርትስት ኑሆ ጎበና እልፈተ ህይወት ከኦነግ የተሰጠ መግለጫ የኦነግ መግለጫ- ጥር 20, 2022

 

 

 

በታጋይ እና አርትስት ኑሆ ጎበና እልፈተ ህይወት ከኦነግ የተሰጠ መግለጫ የኦነግ መግለጫ- ጥር 20, 2022

ጓድ ኑሆ በምስራቅ ኦሮሚያ ላጋ ሚጤ ጃርሶ በ1948 ከእናታቸው ወይዘሮሮ ፋጡማ ሀሰን እና ከአባታቸው አቶ መሀመድ ጎበና ተወለዱ። ከልጅነቱ ማቀንቀን የጀመረው ጓድ ኑሆ በብሔርተኝነቱ ለእስራት ፣ ለስደት እና እንግልት ሲዳረግ ቆይቷል። ጓድ ኑሆ የመጀመርያ የዘፈን አልበሙን ጂቡቲ በስደት ላይ ሆኖ የሰራ ሲሆን የሁለተኛውን ደግሞ ከጓደኛው ኤሌሞ አሊ ጋር በመሆን ሳውድ አራቢያ ውስጥ በመስራት ለኦሮሞ ትግል መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክቷል። ከዘፈን ባለፈ በስደት በሚኖርባቸው የተለያዩ ሀገራት ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት የኦሮሞ ብሔርተኝነትን በማሳደግ እና በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል።

በህዝቡ ዘንድ የተወደደ እና ህዝቡን በጣም የሚወድ ታጋይ ኑሆ በ1991 ደርግ ከወደቀ በኋላ በነበረው የሽግግር ወቅት ኦነግ ያደረገለትን ጥሪ ተቀብሎ ከካናዳ በመምጣት ብዙ የትግል ዘፈኖችን በማቀንቀን ህዝቡን ሲያነቃቃ ነበር። ከዛም በኋላ ከካናዳ እስከ ኤርትራ በመምጣት የኦነግ ሰራዊትን በማበረታታት እና ለነጻነት ትግል የሚቀሰቅሱ ዘፈኖችን በማቀንቀን ረገድ ጉልህ አስተዋጾ ነበረው። ታጋይ ኑሆ ጎበና የስድስት ልጆች አባት ነበር። ታጋይ ኑሆ በህይወት በኖረባቸው ዘመናት የኦሮሞ ህዝብ አንድነትን እየሰበከ ለቆመለት የነጻነት ትግል ህይወቱ እስካለፈችበት ቀን ድረስ በጽናት የቆመ ጀግና ነበር። በመጨረሻም ባደረበት የነርብ ህመም የተነሳ ለረጂም ጊዜያት በህክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ በጥር 18/2022 አዳማ በሚገኘው ቤታቸው ወስጥ አርፍዋል። በአርትስት እና ታጋይ ጓድ ኑሆ መሀመድ ጎበና ከዚህ አለም በሞት መለየት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል። ጓድ ኑሆ ጎበና በኦነግ በሚመራው የኦሮሞ ትግል ውስጥ ታሪክ የማይረሳው ትልቅ አሻራ አሳርፎ አልፍዋል። በመጨረሻም ኦነግ ለቤተሰቦቹ ፣ዘመዶቹ ፣ ጓደኞቹ እና ለመላው የኦሮሞ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል።

ድል ለሰፊው ህዝብ! ጥር 20 2022 ፊንፊኔ