ያለ አግባብ ለሚጠፋው የሰዉ ሕይወትና ንብረት ተጠያቂነት ልኖር ይገባል
(የኦነግ መግለጫ – ጥቅምት 30, 2018)
የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነታችንንና በሕዝቡ ዉድ መስዋዕትነት የተግኘዉ የለዉጥ ሂደት በኣስተማማኝ መልኩ ስር በመስደድ ስኬታማ እንድሆን በማድረጉ ሂደት ላይ የሚሰራ ኣንድ የጋራ ኮሚቴ መስርተን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። በዚህ የጋራ ኮሚቴ አመካይነትም በቋሚነትና በቀጣይነት ተገናኝተን እየተመካከርን በመስራት ላይም እንገኛለን።
ይህንን ሂደት የሰዉ ሕይወት መስዋዕትነትን በማይጥይቅ መልኩ፣ በሀገርና በሕዝብ ንብረት ላይም ጉዳትን በማያስከትል ሁኔታ፣ እንድሁም፣ ያለምንም ጥድፍያና ወከባ ጊዜ ወስደን በመመካከርና በቀና መንፈስ አብረን በመስራት ማሳካት እንደሚቻል የድርጅታችን የኦነግ ጽኑዕ እምነታችንና ኣቋማችንም ነዉ።
ይሁን እንጂ በመንግስት ኣንዳንድ ኣካላትና ግለ-ሰቦች እንድሁም በኢሕአዴግ በቀጣይነት የሚካሄዱብን ኣፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎችና ገደብ ያጡ ሸርና ደባዎች የሕዝቡንና የሀገርን ሰላም የሚጎዱ ስለመሆናቸዉ በግልጽ የሚታይ ሓቅ ነው። ስለሆነም እንደነዚህ ኣይነቶቹን ሸርና ደባዎች፣ እንድሁም ኣፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች በሚመለከታቸዉ ኣካላት ኣስፈላጊ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎባቸዉ ማስቆም እንደሚገባ እስከዛሬ ስናስገነዝብ ቆይተናል። ይህንን ያደረግነው ተስማምተን የገባንበትን የሰላምና የእርቅ ሂደት በስኬት ለማጠናቀቅ ይረዳ ዘንድ መሆኑን ማስገንዝብ እንወዳለን። ይህ ደግሞ ለሕዝብና ለሃገር ሰላምና ደህንነት በቅንነት ከማሰብም እንደሆነ ልታወቅ ይገባል።
ይህ በንድህ እንዳለ ምክንያቱን በትክክል ለመረዳት አዳጋችና ኣስቸጋሪ በሆነብን ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ሃገር በጠላት የተወረረች ይመስል ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የጦር ሠራዊቱን በሕዝባችን ላይ በማዝመት ሰላማዊ ሰዎችን መግደልና የሰዎችን ንብረት መዝረፍ ዛሬም ድረስ ቀጥሎበታል። ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ በቄሌም ወለጋና በጉጂ ዞን ኣከባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉት ሁኔታዎች ለዚህ ጉልህ ማስረጃ ናቸዉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ ክቡር የሰዉ ህይወት ያለ ኣግባብ እንድጠፋ፣ እንድሁም የሕዝብና የሃገር ንብረት እንድወድም፣ ኣልፎ ተርፎም ሕዝቡ በስጋት፣ በጥርጣሬና በፍርሃት ድባብ ስር እንድኖር እያደረገ ይገኛል።
ኣሁን ባለዉ ሁኔታ በጦርነትና በሓይል መፍትሔ ልገኝለት የሚችል ችግር እንደሌሌና ለሕዝብም ሆነ ለሃገር ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ ወይም ጥቅም እንደሌሌ ኦነግ በጽኑዕ ያምናል። በሕዝቡ ትግልና መስዋዕትነት በተግኘዉ የለዉጥ ሁኔታ ላይ እንቅፋት ልሆንና የሕዝቡን ተስፋ ልያጨልም የሚችል ይህ ኣሳዛኝ ኣካሄድ በኣስቸኳይ እንድቆምም እንጠይቃለን። ይህ ኣካሄድ በሚያስከትለዉ ኣደጋ ለሚደርስ የሰዉ ህይወት መጥፋት፣ እንድሁም በሕዝብና በሃገር ንብረት ላይ ለምደርስ ዉድመት ሃላፊነት/ተጠያቂነት ልኖር እንደሚገባም ኦነግ ኣጥብቆ ያሳስባል።
ድል ለኦሮሞ ሕዝብ !
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ጥቅምት 30, 2018