በገሃድ ያልታወጀ ጦርነት በኦነግ፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና በቄሮ ላይ

 

በገሃድ ያልታወጀ ጦርነት በኦነግ፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና በቄሮ ላይ
(በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የተሰጠ መግለጫ)

የኢትዮጵያ ኢምፓዬር ውስጥ ለረጅም ጊዜያት እየተቀያየረ ዛሬን በደረሰው የጦርነትና የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የወያኔ መንግስትና ቅጥረኛ ኣጋሩ የሆነው ኦፒዲኦ ላለፉት 27 ዓመታት የተለያየ መልኮች ያለው ጦርነቶችን መክፈቱ ይታወሳል። የቅርብ ጊዜው የኢትዮጵያ የፖለቲካና የጦርነት ሁኔታን ከተመለከትን ደግሞ በተለያዩ መልኩ በገሃድ ያልታወጀ ጦርነት በኦነግ ላይ እየተካሄደ ስለመሆኑ የሚያስተውለው ብቻ ነው የሚገነዘበው።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በጠላቶቹ ተነጣጥሮበት በበርካታ መልኮች ለተከፈተበት ጦርነት በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት እራሱን በመቆጠብ የነጻነት ትግሉን በማፋፋም የኦሮሞን ህዝብ የሃገር ባለቤትነትና መብቱን እንዲጎናጸፍ በማድረጉ ላይ ኣተኩሮ ነበረ፥ ዛሬም ይህንኑ እየተገበረ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ጠላት በኦሮሞ ላይ የሚያካሄዳቸው የተለያዩ መልኮች ያሏቸው ስውር ዘመቻዎች ኣድማሳቸውን እያሰፉ፣ ስልትና ዘዴ እየቀያየሩ ሲጠናከሩ እነሆ ዛሬ ላይ ደርሰናል።

1. የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፡ በኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግልና በኦነግ ላይ እየተካሄደ ያለ ዘመቻ ኣካል የሆነው በኦነግ/በኦሮሞ ባንዲራ ላይ የሚነዛ ፕሮፓጋንዳ በስርዓቱ የተለያዩ መድረኮች ላይ በኦፒዲኦ ሹማምንት እንዲሁም በኦፒዲኦ/ኢህኣዴግ ቁጥጥር ስር ባሉ እንደኦ.ቢ.ኤን በመሳሰሉ ሚዲያዎች ላይ በግልጽ ሲካሄድ እንደነበር ከኦሮሞ ህዝብ የተሰወረ ኣይደለም።

2. ዘመቻ በኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ላይ፡ የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ጎራ ንቅናቄ የኦሮሞን ኣንድነት ይበልጥ በሚያጠናክር መንፈስና ክንድ መካሄዱ ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በግልጽ እየታየ ባለበትና እንደኦፒዲኦ ያሉ ኣካላትም ውጤቱን ሊክዱ በማይችሉበት በዚህ ወቅት፡ የወገንን የነጻነት ትግል ጎራ በማጠናከርና የሰከነ እንዲሆን በማድረጉ እንዲሁም የጠላትን ጎራ በማዳከሙና መሰረቱ እንዲናጋ በማድረጉ ውስጥ ድርሻ ባላቸው የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል መሪዎች ላይ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑ የኢህኣዴግ/ኦፒዲኦን ጠላትነት በግልጽ የሚያሳይ ነው። በኣሁኑ ወቅት የኦሮሞን ህዝብ የነጻነት ትግል በተለይም ደግሞ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የትጥቅ ትግል ለማሳነስ፣ በማጥላላት ገጽታውን ለማበላሸት፣ መሳለቂያ በማድረግና በማዋረድ እንደለማ መገርሳ ባሉ የኦፒዲኦ ሹማምንትና በኢትዮጵያ መሪዎች ያለኣንዳች ሃፍረት በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች ላይ ኣፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎችና ስድቦች እየተካሄዱ መሆናቸው ከኦሮሞ የተደበቀ ኣይደለም።

3. ብሩህ ታጋዮችና በትግሉ ውስጥ ድርሻ ኣላቸው ብለው የጠረጠሯቸውን መሪዎች የማደን የወያኔ የደህንነት ኣካላት ዘመቻ፡ በኦሮሞ ብሄርተኞችና ታጋዮች ላይ የማደን፣ የእስራትና የሰቆቃ ዘመቻ ፊንፊኔን ጭምሮ በመላው ኦሮሚያ ውስጥ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። ይህ በእጅጉ የተጠናከረው የማደን ዘመቻ የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት ሲፈጸምበት የነበረ ከመሆኑ የተነሳ ኣዲስ ባይሆንም በኣፋቸው የተሃድሶ ጊዜ ነው እያሉ በሚለፍፉበት በዚህ ወቅት ውስጥ መካሄዱ የተሃድሶውን ዓላማ የሚጠቁም ሲሆን ወዴት እንደሚሄድ የምናየው ይሆናል።

4. በሽምግልና ሽፋን፡ የወያኔ ስርዓትና ኦፒዲኦ በሌላ መልኩ እያካሄዱት ያለው ዘመቻ ደግሞ የሃገር ሽማግሌዎችና ኣዛውንትን በመያዝ በኦነግ በሚመራው የትጥቅ ትግል ላይ በማነጣጠር የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ለማፍረስ የታቀደ ዲስኩር መንዛትና ማስነዛት ነው። በዚህም በደቡብ ኦሮሚያ በኩል የደቡብ ዞን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ከተቻለላቸው እጅ እንዲሰጥ ለማድረግ፣ ካልተቻለ ደግሞ ህዝባዊ ድጋፍ ነፍገው በጦር ዘመቻ ለማጥፋት እየተሰራ እንዳለ በኣካባቢው የሚገኘው የኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም በጎረቤት ኬኒያ ያለው የኦሮሞ ማህበረሰብ ምስክር ነው።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን እናጠፋለን ብለው እያሴሩና እየዘመቱ ያሉት እነዚህ ኣካላት ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት የቆሙ ቢሆኑ ኖሮ የኦሮሞን ህዝብ ከምድረ-ገጽ እያጠፋ ያለውን የደህንነት፣ የጦር ሃይልና የሶማሌ ልዩ ሃይል ትጥቅ ያስፈቱ ነበር። ይህ ዘመቻ በሽምግልና ሽፋን በኬኒያና በኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ ኦሮሞዎች ላይ በስፋት ከተከፈተ እነሆ ሁለት ወራትን ኣስቆጥሯል።

የወያኔ መንግስት ከቅርብ ጊዜያ ወዲህ በስውር ሲያካሄድ የነበረውን ዘመቻ ኣሁን ደግሞ ገሃድ በማውጣት በኦነግና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ላይ በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ የፖለቲካ ዘመቻውን በኣዲስ መልክ ለማካሄድ ማቀዱ በተለያዩ ኣቅጣጫዎች እየተደረጉ ያሉ ስምሪቶች ይመሰክራሉ። ኣቶ ለማ መገርሳ ደምቢ-ዶሎ ላይ ያደረገ ንግግር ስርዓቱ የስውር ዘመቻ ዋዜማ ላይ መሆኑን ያመላከተ ነው። ለዚህም ኣቶ ለማ “ለሁለትና ሶስት ወራት ከጫካ ትተኩሱ ይሆናል ግን ሃይል ያለው ነው መጥቶ የሚያጠፋችሁ” በማለት የትጥቅ ትግሉን በተለይም ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በማስመልከት የተናገረውና ንቀትና ስድብ የቀላቀለ ንግግሩ ከሁሉም ጆሮ የደረሰ ኣብይ ምስክር ነው።

የኢህኣዴግ ቡድንና ኦፒዲኦ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ላይ ግልጽ ያልሆነ ዘመቻ ስለመክፈታቸው የሕወሃት የጦርና የደህንነት ሃይሎች እንዲሁም በክልልና በወረዳ ደረጃ ያሉ የኦፒዲኦ ሹማምንትን ያቀፈ የሕወሃት ታማኞች ቡድን በደቡብ ኦሮሚያ ያአ-በልኦ ላይ እንዲሁም በምዕራብ ቄሌም ወለጋ ላይ በመሰማራት ሰፊ እቅድ ይዘው መንቀሳቀሳቸው በግልጽ ያሳያል። በዚህ ዘመቻ እቅድ መሰረት በያኣ-በልኦ ከ13ወረዳዎች የተውጣጡ 42 ሰዎች ‘በኦነግ ጉዳይ ላይ ጉባዔ ማካሄድ’ በሚል ከላይ ኢህኣዴግ/ኦፒዲኦ በሰጣቸው ዓላማ ላይ በውይይት ላይ ናቸው። የውይይት ዓላማም ግልጽና ኣጭር ነው። በህዝቡ ላይ የፖለቲካ ዘመቻ በማካሄድ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ጠላት እንዲገባ ግፊት ማድረግ፣ እምቢ ካለ በሃይል/በጦርነት ከኣካባቢው ማስወጣት። በምዕራብ ኦሮሚያ በኩልም በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ካሉ የኦፒዲኦ ሹማምንት ሶስት-ሶስት ሰዎችና ኣስተዳደሮች እንዲሁም የልዩ ሃይሎችና የኣድማ-በታኝ ሃይሎችን ያቀፈ ‘የቄሌም ወለጋ ዞን ኣጽጂ ኮሚቴ’ የተሰኘ ቡድን ለተመሳሳይ ዓላማ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ ገብቷል። ከዚህም ሌላ በኦነግ ኣመራሮችና መዋቅሩ ላይ በተለያዩ መልኩ ዘመቻ ለማካሄድ የተለያዩ ቅድመ-ዝግጅቶች በስውር በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።

ጥሪ! ለኦሮሞ ህዝብ፡ የኦነግ ኣባላት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና የቄሮ ብሊሱማ ኦሮሞ ኣባላት የኦሮሞን ህዝብ የሃገር ባለቤትነት መብት ለማስከበር፣ ለህዝቡ ነጻነትና ለሃገሩ ኦሮሚያ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ከባድ መስዋዕትነት የጠየቀ ያልተቋረጠ ፍልሚያ በማፋፋም የኢትዮጵያ መንግስት፡ የጀሌዎቹና ኣጫፋሪ ኣጋሮቹን ዘመቻ ስንመክት ዛሬን እንደደረስን ከናንተ የተሰወረ ኣይደለም። የኦሮሞ ህዝብና መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ያስገኘው ድል ትሩፋት ተቋዳሾች መሆናቸው ግልጽ ነው። ዛሬ ትላንት ኣንተንና ልጆችህን ሲያስጨርሱና ለሰቆቃ ሲዳርጉ የነበሩት ኣፋቸውን ማር ቀብተው በኦነግ-ቄሮ መሪነት ኣሁን ካለበት ደረጃ ባደረስከው የነጻነት ትግልህ ላይ እየዘመቱ ባሉበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ስለሆነም የተገኘውን ድል በማስጠበቅና የኢህኣዴግ/ኦፒዲኦ ቡድን በኣዲስ መልክ እየከፈተ ያለውን ዘመቻ ኣስፈላጊና ኣመቺ መሆነ ሁኔታ ሁሉ እየቀለበሰ የኦሮሞን ህዝብ የነጻነት ትግል ወደፊት ለማራመድ እራስህን ማዘግጀት ግዴታ መሆኑን እናሳስባለን።

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የኦሮሞ ህዝብና ኦነግ ለረጅም ዓመታት ባካሄደው ትግል በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ተጨቋኝ ህዝቦች ጥቅምና ፍላጎት ሁሉ ታላቅ ክብር እንዳለው ለበርካታ ዓመታት ባካሄደ ንቅናቄ ውስጥ በተግብር ያሳየ መሆኑን ሁሉም ይመሰክራል። እኛም እንዲሁ በሃገሪቷ ውስጥ ካሉ ተጨቋኝ ሁሉም ህዝቦች የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ክብርና የትግል ድጋፍ እንጠብቃለን። ኣሁንም የኦሮሞን ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም በሃይል ለማፈን ኣያሌ ደባዎ እየተፈጸመ ስለሆነና ደም መፋሰሱ ሊቀጥል ስለሚችል የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህንን ተገንዝበው ከኦሮሞ ህዝብና ከትግሉ ጎን እንዲቆሙ ኦነግ ጥሪውን ያቅርባል።

ለኢትዮጵያ መንግስት ሹማምንት፣ ለኦሮሚያ ክልል መንግስት ባለስልጣናትና ከበስተጀርባው ላሉ ሃይሎች በኦነግና በኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ላይ ከኣንድ ምዕተ-ዓመት በላይ ከተካሄደው በስተቀር ላለፉት 27 ዓመታት ሙሉ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ኣያሌ የህዝብ ልጆች በተለይም የኦሮሞ ደም ፈስሷል። በዚህ ውስት የኦፒዲኦ ባለስልጣናትና ሹማምንት ድርሻ ምን እንደሆነ የኦሮሞ ህዝብ ያውቃል። በቀጣይነት እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ለሚደርሰው ደም መፍሰስና ኣደጋ ተጠያቂነቱ የፌዴራልና የክልል መንስግት ባለስልጣናት እንዲሁም ከነሱ በስተጀርባ ያሉ ሃይሎች መሆኑን ኦነግ ኣጥብቆ ያሳስባል።

ኦነግ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር መፍትሄ በተመለከተ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ባጠቃላይ ለበርካታ ዓመታት የቆየውን ዘርፈ-ብዙ ቀውስ ከመሰረቱ ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ሃገሪቷንና ህዝቦችን ኣንቆ ወደፊት እንዳይራመዱ ጠፍሮ የያዛቸውን ችግር ከመፍታት ይልቅ፡ በሃገሪቷ ብዙሃን የሆነው ህዝብ መሪ ድርጅት በሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ላይ በማነጣጠር በግልጽና በስውር በመዝመት ከፍተኛ ኣደጋ እያስከተለ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ ከማወሳሰብ ባሻገር ኣንዳችም ፋይዳ የለውም። ከዚሁ ጋር በኢትዮጵያ ለህዝቦች መብት መከበርም ይሁን ባጠቃላይ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት እንቅፋት የሆነውን የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ መልኩ በመደገፍ ላይ የሚገኘው የዓለም ማህበረሰብ ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲና ለነጻነት ሲል ውድ መስዋዕትነት እየከፈለ ካለው የኦሮሞ ህዝብና የኣካባቢው ህዝቦች ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናድሳለን። በኦነግ፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና በቄሮ ቢሊሱማ ላይ ሰሞኑን እየተካሄደ ያለው በግልጽ ያልታወጀው ጦርነትም የማይሳካ መሆኑን ኦነግ በድጋሚ ማረጋገጥ ይወዳል።

ዘመኑ የጭቆና ፍጻሜ ዘመን ነው! ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ሰኔ 2 ቀን 2018ዓም