በኢትዮጵያ በህዝቦች መካከል ግጭት መፍጠር የመንግስታዊ ሽብርተኝነት ተግባር ነው!

በኢትዮጵያ በህዝቦች መካከል ግጭት መፍጠር የመንግስታዊ ሽብርተኝነት ተግባር ነው!

Itoophiyaa

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ከኣፋር ነጻነት ግንባር ፓርቲና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የተሰጠ የጋራ መግለጫ

መጋቢት 28, 2018 ዓም

ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው የሕወሃት/ኢሕኣዴግ ስርዓት ፍጻሜው የተቃረበውን ኣገዛዙን እስትስፋስ ለማቆየት የተለያዩ ከንቱ ጥረቶችን ተያይዟል። ህዝቦች ለነጻነትና ለዲሞክራሲ እያካሄዱ ባሉት ተግል መሰረቱ የተነቀነቀውን የቡድኑን የበላይነት የማስጠበቅ ስርዓት መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የተቻለለትን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ከለላ የስርዓቱ የታጠቁ ሃይሎች ንጹሃን ዜጎችን መግደል፣ ኣፍነው መሰወርና ለከፋ ሰቆቃ መዳረጋቸውን ቀጥለዋል። ይህ ኣምባገነን ቡድን የህዝቦችን የትኩረት ኣቅጣጫ ሃገሪቷን እያመሰቃቀለ ካለው ቀውስ ለማስቀየርና ህዝቦችን በኣገዛዙ ላይ ያለማቋረጥ እያካሄዱት ካለው ተቃውሞና ፍልሚያ ለመግታት በማለም ለዘመናት በሰላም፣ በመከባበርና በመፈቃቀር ኣብረው በኖሩ ህዝቦች መካከል የመጠራጠርና የጥላቻ መርዝ ለመርጨት እየሰራ ነው።

በዚህም የሕወሃት/ኢሕኣዴግ ቡድን በኦሮሞና በኦጋዴን-ሶማሌ ህዝቦች መካከል የፈጠረው ግጭት የኣያሌ ዜጎችን ህይወት መቅጠፉና ከሁለቱም ወገን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬኣቸው መፈናቀላቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ስርዓቱ ይህን መሰል ጥፋት በህዝቦች ላይ ፈጽሟል፥ ይህን እኩይ ዓላማውን ኣሁንም በመቀጠል በየዕለቱ የሰብዓዊ ወንጀል እየፈጸመ ነው።

የኣፋር ነጻነት ግንባር ፓርቲና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኢሕኣዴግ ሃይሎች እራሳቸውን በመደበቅ በምስራቅና ሰሜን-ምስራቅ የኦሮሚያና የኣፋር ክልል ኣዋሳኝ ድንበር ላይ በሰላማዊ መንገድ ኑሮኣቸውን ሲመሩ በነበሩ ሲቪሎች ላይ በሁለቱም ወገን ጥቃት ሊያደርሱ መሞከራቸውን ኣረጋግጠዋል። ይህ ሰሞኑን የተፈጸመውና በኣካባቢው ነዋሪዎች የተረጋገጠው የወያኔ/ኢሕኣዴግ ድርጊት ስርዓቱ በመላው ሃገሪቷ ስርዓቱ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን ለማናቆር ሲፈጽመው የነበረው ተመሳሳይ ድራማ መሆኑ ግልጽ ነው።

ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ስርዓት በሃገሪቷ ውስጥ ያሉ ህዝቦችን ከፋፍሎ እነሱ በጋራ ክንድ ለነጻነት፣ ለሰላምና ለዲሞክራሲ እያካሄዱት ካለው ትግል ለማዳከም የተቻለለትን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል። ይህን ጸረ-ህዝብ ዓላማውን ለማሳካትም ህዝቦችን ከፋፍሎ ለመግዛት በሁሉም ስልቶች እየተጠቀመ ይገኛል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኣፋር ነጻነት ግንባር ፓርቲ በሁለቱ ህዝቦች ኣንድነት ላይ በማነጣጠር እየተፈጸመ ያለውን ሴራና ጥረት ኣጥበቀው ያወግዛሉ፡ ይጋፈጣሉ። ሁለቱም ድርጅቶች የኣፋርና የኦሮሞን ህዝቦች ግንኙነት የሚያዳክም ማንኛውንም ድርጊት ለመጋፈጥ ያላቸውን ኣቋም በድጋሚ ይገልጻሉ።

ስለሆነም የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኣፋር ነጻነት ግንባር የኣፋር ህዝብና የኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም ሌሎችም የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህንን የወያኔ/ኢሕኣዴግ እኩይ ዓላማ ኣስቀድመው እንዲገነዘቡ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ። ይህ የኣገዛዝ እድሜው ኣልቆ ከመቀበሪያው ኣፋፍ የሚገኘው ኣምባገነን ስርዓት ተስፋ በመቁረጡ፡ ቡድኑን ስልጣን ላይ ለማቆየት ሲል ማንኛውንም ኣይነት ወንጀል ከመፈጸም ወደኋላ ኣይልም።

በመሆኑም የኣለም ማህበረሰብ የወያኔ/ኢሕኣዴግ ቡድን ማለቂያ የሌለው ግጭትን በህዝቦች መካከል ከመፍጠር ተቆጥቦ የህዝቦችን የበላይነትና የሃገር ባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ ሁሉን-ቀፍ እርምጃ እንዲፈልግ ጫና እንዲያሳድሩበት እንጠይቃለን።

በመጨረሻም የኣፋር ህዝብ፣ የኦሮሞ ህዝብና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሌሎችም ህዝቦች የሕወሃት/ኢሕኣዴግ ወያኔ መንግስት በመካከላቸው የሚሸርበውን ሴራ በንቃት በመጠበቅ፡ ስርዓቱ የሚፈጥራቸውን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን። ከዚሁ ጋር ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የህዝቦችን ግንኙነት የሚያውኩ የወያኔ/ሕወሓት እኩይ እንቅስቃሴዎችንና ተግባራትን ህዝቡን በማስገዘብ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲወጡና በጋራ ክንድ በመታገል ሰው-በላውን ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ስላም ያሸንፋል!!

የኣፋር ነጻነት ግንባር ፓርቲ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር

መጋቢት 28, 2018 ዓም