የተወዳጁ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ 1ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የተሰጠ መግለጫ -ሰኔ 28፡ 2021ዓም የኦ ነ ግ መግለጫ- ሰኔ 28፡ 2021ዓም
የተወዳጁን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ 1ኛ ዓመት ስናከብር የህዝባቸውን ሃቅ ኢፋ ለማውጣት ድምጽ በመሆናቸው ብቻ በኢትዮጵያ ስርዓት በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ የተፈጸመባቸውንና እስከ አሁን የት እንዳሉ ሳይታወቅ የተሰወሩትን አያሌ ውድ የህዝብ ልጆችንም አብረን መዘከርና ታሪካቸውን ከፍ አድርገን ማውሳት አስፈላጊ ነው። መልከ-መልካም፣ በአርት ጥበብ በተላበሰ መልኩ የህዝባችንን አንድነት፣ ባህል፣ እንዲሁም ጨቋኙ ስርዓት በህዝባችን ላይ ያደረሰውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በግጥምና በዜማ አዋዝቶ እጅግ በሚስረቀረቀውና ቀልብ በሚስበው ድምጹ የህዝቡ ድምጽ በመሆን በወገኑ ላይ የሚደርሰውን በደል ለህዝቡ ሲያሳይና ለነጻነት ትግል ሲያነቃቃ የነበረው ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ ዛሬ አንድ ዓመት አልፏል። ሰኔ 29 ሃጫሉ የተገደለበትን ቀን፣ ተከታታይ የኢትዮጵያ ስርዓቶች የፖለቲካ ጥቅማቸው ለመስጠበቀ እና ለጊዜያዊ ስልጣን ብለው ሲገድሏቸውና ሲሰወሯቸው ከነበሩት ታጋዮች፣ አርቲስቶችና ደራስያን መካከል እንደ አብዲላሂ አርሲ፣ አዩብ አቡበከር ፣ አቡበከር ሙሳ፣ ሙስጠፋ አብዲ(ሐረዌ)፣ አህመድ ከቢራ፣ አያንቱ ቦረና፣ ሂሜ ዩሱፍ፣ ኩለኒ ቦሩ፣ ሰቦንቱ በሬንቱ፣ ጅሬኛ አያና፣ ኤቢሳ አዱኛ፣ ጠና ወዬሳ፣ ኡስማዮ ሙሳ፣ አብዲ ቆጴ፣ በዓሉ ግርማ፣ ዘኑ መኮንን፣ ዮሴፍ ገመቹ፣ ማረሜ ሀርቃ፣ ዳዲ ገላን፣ ጨዋቃ ያዴሳ እና ወዘተ. በህዝባቸው ላይ የሚደርሰውን በደል ስላጋለጡ ብቻ የተገደሉትንና ከፊሎቹም የተሰወሩትን የምናስታውስበት ቀን ነው። እውቁ የኦሮሞ አርቲስትና ታጋይ ሃጫሉ ሁንዴሳም ለህዝባቸው መብት መከበር ሲሉ ውድ የህይወት ዋጋ የከፈሉትን አርቲስቶች አደራ ተሸክሞ በዘፈን አርት፣ የኦሮሞን ባህልቋንቋ፣ ማንነት፣ ታሪክና ወግ በማሳደጉ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ሲያበረክት ቆይቷል። በተለያዩ መድረኮች ላይ የኦሮሞን መሬት መቀራመት፣ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት፣ በኦሮሞ ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና የባርነት ቀንበር በዜማ አዋዝቶ በማጋለጥ ገሃድ ሲያወጣ ነበር። ኦሮሞ በጠላት የተነጠቀውን ሃቁን እንዲያስመልስ፣ የተደበቀውን ታሪኩን አጉልቶ እንዲያወጣ፣ ለመብቱ ተፋልሞ የባዕዳንን የጭቆና ስርዓትን ታግሎ እንዲያስወግድ በዘፈን አርት በማነሳሳትና በማንቃት ሃጫሉ በወዳጅም በጠላትም ዘንድ ከፍተኛ እውቅና ያለው ጀግና ነው።
ሃጫሉ ላመነበትና ‘ለህዝቤ ይሆናል’ ያለውን ያለአንዳች ሃፍረትና ፍራቻ በጀግንነት ተናግሮ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ባርነትና በደል ስለሚናገር በመላው የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ፍቅርና ክብር አለው። በተቃራኒው ደግሞ ኦሮሞን ለባርነት ዳርገው ሃብቱንና መሬቱን መውረስ የሚሹ የኦሮሞ ትግል ጠላቶችን ሴራ አጋልጦ ህዝቡን ስለሚቀሰቅስባቸው፣ የሃሰት የታሪክ ትርክትን አገልጦ ውሸትን ቦታ አሳጥቶ እውነታውን አፍረጠጦ ስለሚናገር በኦሮሞ ትግል ጠላቶች ዘንድ በእጅጉ ይጠላል። በኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ውስጥ የህዝብ መብት ታጋይ በመሆን ከፍተኛ ድርሻ ሲወጣ የነበረው፣ ህዝቡ እንደአይኑ ብሌን የሚያየውን ይህን ጀግና ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም በመግደል በግድያው አስሳቦ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን አመራሮች፣ መኮንኖች፣ አባላትና ደጋፊዎችን በጅምላ ወደ እስር ቤት ማጋዝና ከፊሉን ደግሞ ገድሎ መሰወር የታሪክ ጠባሳና ይህንን የምንዘክርበት ቀን ነው። ከአርቲስት ሃጫሉ ግድያበኋልስ በርካታ አርቲስቶች ስልጣን ላይ ባለው ቡድን በመታሰር ዛሬም በእስር ቤትና የጦር ካምፕ ውስጥ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይገኛል። እንደ ፈልመታ ከበደ፣ ሰብኬበር ደሜ፣ አደም ካዎ፣ ፈልመታ ባልቻ፣ ደሚሶ ሞሲሳ፣ ደራሲ ለሊሳ አባተን የመሳሰሉት ያለአንዳች ጥፋት በጠላት ታስረው እየተሰቃዩ ያሉ ናቸው። ደራሲ ኦፍታና ተሬሳ እስከ ቅርብ ጊዜ በምዕራብ ሽገር ጊንጪ ከተማ ታስሮ ከቆየ በኋላ ስልጣን ላይ ባለው የብልጽግና ጦር ተገደለ። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፉ ጸረ-ዲሞክራሲ እርምጃ በመሆኑ እናወግዛለን። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ይህን ሃዘን ዘወትር እያስታወሰ የሃጫሉን ግድያ የፈጸሙት የተካሄደውን ምርመራ ጨምሮ ለገለልተኛ አካል ኢፋ ሆኖ ለህዝብ ተኣማኒ በሆነ መልኩ ለህግ ውሳኔ እንዲቀርብ አበክሮ ይሰራል። በተለያዩ ቦታዎች ሰቆቃ እየደረሰባቸው የሚገኙ አርቲስቶች ያለ አንዳች
ቅድመ-ሁኔታ በትግላችን ሊለቀቁ በሚችሉበት ሁኔታ እንዲታገል ህዝባችንን ልናስታውስ እንሻለን። በመጨረሻም ሃገሪቷን የገጠማትን ውስብስብ ችግር በመፍታት ወደ ሰላምና እኩልነት ለመመለስ ሁሉን-አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ተካሂዶ አንድ አድን መንግስት መመስረት እንዳለበት ስንገልጽ ቆይተናል። አሁንም ይህንኑ በድጋሚ አበክረን እየገለጽን፥ የኦሮሚያ ዜጎች የሰላማቸው ዋስትና ለሆነው የኦሮሚያ ክልል ብሄራዊ የሽግግር መንግስት በጋራ በመሆን ድጋፋቸውን እንዲለግሱ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን። ታጋይ ይሰዋል፥ ትግሉ ይቀጥላል!. ድል ለሰፊው ህዝብ! የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ሰኔ 28፡ 2021 ዓም
ፊንፊኔ