በአሁኑ ወቅት እየተከሄደ ያለውን ህገወጥ ጠቅላላ ጉባኤን በተመለከተ የኦነግ መግለጫ

Obsi

መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም                                                                                                                                                                         No:A6112/2011

ጥቂት አፈንጋጭ ቡድን በ ውጫዊ አካል አደረጅነት እና የፋይናንስ ድጋፍ በድርጅታችን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ኦነግ/ አመራር አባላት ስም በፈጠሩት ውዥንብር፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን ውዥንብር ለማጥራት እና በተለይም በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ተፈጠረ የተባለውን አለመግባባት በተመለከተ ድርጅቱ ባለው ህገ ደንብ እና አሠራር መሠረት በጠቅላላ ጉባኤ እንዲ ፈታ መወሰኑ ይተወቃል። ለዚህም ቀደም ብለው በድርጅቱ ህገደንብ እና የውስጥ አሠራር መሠረት በብሔራዊ ምክር ቤት የተመረጡት የኦነግ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ገብቶ ይህንንም ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ፣ በይፋ በኦፍሴላዊ ደብዳቤ አስተውቋል። በመሀከልም ኮሚቴው የደረሰበት ሁኔታ ለሚመለከታቸው አካላት እየስተወቃ፣ በተጨባጭ ያጋጠሙትን ፈታናዎችንም እንዲቀረፉለት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር። የኦሮሞ ነፃነት ግንባርም ይህን የኮሚቴውን ጥያቄ ተንተርሶ በቀን 18/06/2013 ዓ.ም ለምርጫ ቦርዱ በፃፈው አቤቱታ ለጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አስቻይ እና ምቹ የስራ ቦታ እንዲመቻች የድርጅታችን ዋና ፅ/ቤት እንዲከፈትልን መጠየቃችን የሚታወስ ነው።
በሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያለ አንዳች የፍርድ ቤት ትእዛዝ በሃይል ዋና ፅ/ቤታችንን መዝጋቱ ይታወሳል። ከዚያ ቀን አንስቶ ዋና ፅ/ቤቱ በቅጥር ግቢው ውስጥ እና በዙሪያው የሚካሄደውን ማንኛውንም ተግባራት ለመቆጣጠር ያለ ህግ አግባብ ሀላፊነት በወሰደው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ስር ይገኛል። ነገር ግን፣ በዛሬው ቀን በደረሰን መረጃ ላይ ተመሥርተን ድርጅታችን የማያውቀው ህገወጥ ስብሰባ በዋና ፅ/ቤታችን ሊደረግ መሆኑን አመልክተን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስቀድሞ ከቢሮ ሲያስወጣን በራሱ በወሰደው ሀላፊነት መሠረት በዓይኑ ፊት በአፈንጋጭ ቡድኖች እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ተግባር እንዲያስቆም መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን በፃፍነው ደብዳቤ ጠይቀናል።
በድርጅታችን እምነት በአሁኑ ወቅት በዋናው ፅ/ቤታችን እየተካሄደ ያለው ስብሰባ ሙሉ በሙሉ ለአፈንጋጭ ቡዱኑ ሊፈቀድ የማይገባ ህገወጥ ስብሰባ ነው። ይህን ህገወጥነት እያወቀ ቆሞ የሚመለከት የህግ አስከባሪ አካልም ተጠያቂነቱ እየተወጣ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። እነዚህ አፈንጋጭ ቡድን፣ በኦነግ ስም ጠቅላላ ገባኤ ለመጥረት ሆነ ለብቻቸው ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ምንም ዓይነት ድርጅታዊ ውክልና እና ህጋዊ መሠረት የለቸውም። ይህ አካሄድ የድርጅታችን መተዳደሪያ ደንብንም ሆነ በአዋጅ 1162/11 የተደነገገውን የፖለቲካ ፓርቲ የጠቅላላ ገባኤ ስነስርዓት የተፃረረ ነው። በዚህ ላይ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ያለድርጅቱ ህጋዊ ተወካይ/ ያለሊቀመንበሩ/ እውቅናና ፍቃድ በተለይም ሊቀመንበሩን ጨምሮ ሁሉንም የድርጅቱ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎችን ከህግ አግባብ ውጭ ከዋና ፅ/ቤት በኃይል በስወጣበት ሁኔታ፣ ጥቂት አፈንጋጭ ቡድንን አስጠልሎ ህገወጥ ስብሰባ በድርጅታችን ስም እንዲያካሂዱ ለመፍቃድ ምንም ዓይነት የህግ መሠረት የለውም።

ስለዚህም፣የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ኦነግ/ በድርጅታችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ነገር ህገወጥ፣ ኢፍትሐዊና ፖለቲካዊ ሸፍጥ መሆኑን ለመለው የኦሮሞ ህዝብ፣ ለኢትዮጵያ ህዝቦች እና ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ እያስታወቀ፣ የዚህ ዓይነቱ ግፍም ሀገሪቷን ወደ ከፋ ብጥብጥ ከመውሰድ ውጭ ለማንም መፍትሄ እንደማያመጣ አጥብቀን ለማስገንዘብ እንወዳለን። ለዚህም ህገወጥ ተግባር ዋና ተጠያቂው መንግስት እና ይህን ህገወጥ ተግባር በማስፈፀም ላይ ያሉት የመንግስት ተቋማት በመሆናቸው፣ ቁልፍ የመንግስት የፀጥታ፣ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ተቋማት፣ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን ጨምሮ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው የሀገሪቱን ዜጎች አኩል እንዲያገለግሉ በአፅንዖት እያስገነዘብን፣ በተለይም የአዲስ የአበባ ፖሊስ ኮሚሸን ይህን ግዙፍ የህግ ጥሰት በአስቸኳይ እንዲያርም አበክረን እንጠየቃለን!

በመጨረሻም፣ የድርጅታችን አባላት እና ደጋፊዎች ከዚህ ህገወጥ የማጭበርበሪያ ስብሰባ ላይ ላለመከፈል ለሳያችሁት የሚያስደንቅ ትጋት እያመሰገንን፣ በቀጣይም ከደርጅታችሁ ጎን በመሆን በቁርጠኝነት ድርጅታችሁን እንዲትከላከሉና ዘብ እንድትቆሙለት ጥሪ እናቀርባለን!

ድል ለሰፊው ህዝብ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
ፊንፊኔ