የሀገር ሰላምና የዜጎች ደህንነት ሊረጋገጥ የሚችለዉ ሁሉም ወገኖች ለሁለንተናዊ መፍትሄ ተግተዉ ስሰሩ ብቻ ነው
(የኦነግ መግለጫ – የካቲት 14, 2012)
የክስተቱን መንስዔና አጠቃላይ ምንነቱን አስመልክቶ እስካሁን በቂ ግንዛቤና መረጃ ባይኖረንም እንኳ በትናንትናዉ ዕለት (የካቲት 13, 2012) በቡራዩ ከተማ የተፈጸመዉንና የኮሚሽኔር ሰለሞን ታደሰ ሕይወት የጠፋበትን ግድያና የአካል ጉዳት ያደረሰዉን ጥቃት በጽኑ እናወግዛለን። በጠፋዉ ሕይወትና በደረሰዉ አካላዊ ጉዳት ለተጎዱትም የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለተጎጂ ቤተሰቦችና ጓደኞች ሁሉ መጽናናቱን እንመኛለን።
በእንዲህ መሰሉ ጥቃትም ይሁን በሌላ በምንም መልኩ የተወሰኑ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ዒላማ አድርጎ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና አላስፈላጊ ጫናዎች የሀገሪቱን ችግሮች ይበልጥ ያባብሱና ያወሳስቡ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣሉ ብለንም አናምንም። በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ መንገዶች እየታዩ ላሉት የፖለቲካና የደህንነት ችግሮች ሁሉ ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ መንግሥት ከፍተኛዉን ድርሻና ኃላፍነት እንዳለዉ ይታወቃል። የዚህች ሀገር የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉም ይህንን አስመልክቶ የድርሻቸዉን ለመወጣት ግዴታ አለባቸዉ። ሰፊዉ ሕዝብም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ የተጋረጡብንን ችግሮች በተመለከተ የችግሮቹን መንስዔና መፍትሄያቸዉን ለይቶ ያሉብን ችግሮች ለዘለቄታዉ መፍትሄ በሚያገኙበት አቅጣጫ ላይ የበኩሉን እገዛ ለማድረግ በንቃት መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነዉ ብለን እናምናለን።
ስለሆነም፣ ባሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ላይ አስፈሪና ዘግናኝ የሆነ የስጋት ደመናን አንዣቦ ያሉት የፖለቲካና የደህንነት ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ልያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ለማፈላለግ ሁሉም ወገኖች ኃላፍነትና ግዴታቸዉን በላቀ የተጠያቂነት/responsibility መንፈስ እንዲወጡ ኦነግ አጥብቆ ይማጸናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት የዜጎች ነፃነትና ደህንነት ልረጋገጥበት የሚችለዉ ሁለንተናዊ መፍትሄ ልገኝ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደመንግሥት የተረከበዉን ታሪካዊ ኃላፍነትና ተጠያቂነት መወጣቱ የወሳኝነት ሚና እንዳለዉ ተገንዝቦ ይህንን ኃላፊነቱን በገንቢ ሁኔታ እንዲወጣ በአፅንዖት እናሳስባለን።
ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
የካቲት 14, 2012