አሁን በኢትዮጵያ ለሚታዩ ችግሮች የሕዝቦችን ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድ ብቸኛዉ መፍትሄ ነውአሁን በኢትዮጵያ ለሚታዩ ችግሮች የሕዝቦችን ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድ ብቸኛዉ መፍትሄ ነው
( የኦነግ መግለጫ – ጥቅምት 12 2012 ዓ . ም .)
ኢትዮጵያ የሚትታወቅበትን ወታደራዊ አገዛዝ፣ እንዲሁም፣ የጭቆናና ብዝበዛ ስርዓተ-መንግስትን በመቀየር የሕዝቦችን ነፃነት፣ እዉነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ብሎም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለዘመናት በተካሄደ ትግል ዉስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ከፍተኛ ድርሻዉን ኣበርክተዋል። በተላይ ደግሞ፣ የኢሕአዴግ ስርዓት ላለፉት 27 ዓመታት በተለየ መልኩ እንደ ሕዝብ ለይቶ የግፍ በትሩን ያሳረፈበት የኦሮሞ ሕዝብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢሕአዴግን የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ በተካሄዱ ትግሎች ዉስጥ እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ከባድ መስዋዕትነት የከፈለበት የለም ለማለት ይቻላል።
ይሁን እንጂ፣ ዛሬ ሕዝባችን የብዙ ሺዎች ዉድ ልጆቹን ህይወት፣ ደምና አጥንት ገብሮ ባስገኘዉ ለዉጥ በአግባቡ እየተስተናገደ አይደለም። እንደ ግለ-ሰብም ሆነ በቡድን ወይም በድርጅት ታግሎ በከፈሉት መስዋዕትነት ይህንን ዛሬ የሚናየዉን ለዉጥ እንዲመጣ ያስቻሉት የሕብረተሰቡ ክፍል ተገቢዉን መብት፣ ክብርም ሆነ እዉቅና ተነፍጎ ነገሮች ሁሉ የተገላብጦሽ ሆኑ። ይህም ኣንሶ እነዚህ የሕብረተሰቡ ክፍሎች እንደ ለዉጡ አካል እንኳ መታየታቸዉ ቀርቶ በአንጻሩ እንደ ለዉጡ እንቅፋቶችና እንደ ጠላት እየተቆጠሩ ትናንት በትግሉ መዕበል ታግዞና ተገፍቶ ስልጣን ላይ በወጣዉ ቡድን ተዘመተባቸዉ።
በዚህም ሕዝባችን ዛሬ በመራራ ትግልና በከባድ መስዋዕትነት ባመጣዉ በዚህ ለዉጥ የሰላም፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ አየር ለመተንፈስ የነበረዉ የተስፋ ብርሃን ከመደብዘዙም በላይ የህይወትም ሆነ የዕለት-ተዕለት እንቅስቃሴዉ ሰላምም ከድሮ በባሰ ሁኔታ ለአደጋ የተጋለጠ ሆነ። ዛሬ መላዉ የኦሮሚያ ምዕራባዊና ደቡባዊ ክፍል ሕዝባችን እራሱ ኢሕአዴግ እተዳደርበታለሁ በሚል ሕግና ስርዓት እንኳ እዉቅና ባልተሰጠዉ ወታደራዊ አስተዳደር (Military Command Post) ሥር ከ9 ወራት በላይ እየማቀቀ ስሆን፣ በእነዚህ አከባቢዎች በመንግስት ወታደሮች እየተካሄዱ ያሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ እስራት፣ የአካልና የስነ-ልቦና እንግልትና ሰቆቃ፣ ዝርፍያና አሰቃቂ ግድያዎች ታይቶና ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ እጅግ ዘግናኝ ናቸው።
ባሁኑ ጊዜ በዚህች ሀገር ዉስጥ ከሚገኙት የዜና አዉታሮች መካካል በከፍተኛ ደረጃ የብሔር ጥላቻና አድልዖ በማራመድ የሚታሙ እንኳ እንደልባቸዉ ሃሳባቸዉን እያንሸራሸሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ ሕዝብ የመብት ጥያቄ ላይ በማተኮር የሚሰራዉ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ኦሚኔ/OMN እና ዋና ስራ-አስኪያጁ (Director) ጃዋር መሐመድ ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ዛቻና ማስፈራሪያ ከምን የመነጨ እንደሆነ ከሕዝባችን የተሰወረ ኣይደለም። በአጠቃላይ ለጊዜዉ ምክንያቱን በዉል መለየት ብቸግረንም አንድ ዓመት ከመንፈቅ ባስቆጠረዉ በዚህ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የአስተዳደር ጊዜ ዉስጥ በሕዝባችን ላይ የሚደርስ እሮሮ በይበልጥ እየከፋ፣ ፍትሃዊ ጥያቄዉና ድምጹም ከምንጊዜዉም በላይ እየተናቀና ወደጎን እየተተወ መምጣቱ በግልጽ እየታየ ነዉ። ይሁንና ሕዝባችን የዘመናት ትግሉን ዉጤት በዜሮ ኣባዝቶ ትግሉንም ወደኃላ ለመመለስ የሚኬደዉን ይህንን አስጸያፊ ሁኔታና አካሄድ በምንም ተዓምር ዕድል አይሰጠዉም። እናም ይህ ሁኔታ በጊዜ ካልታረመና ከቀጠለ እስካሁን ካደረሰዉ ጉዳትና የሰላም መደፍረስ ይልቅ የወደፊት አቅጣጫዉና የሰነቀዉ ጥፋት የሚያሰጋ ሆኖ ይታየናል።
በእኛ እምነት እነዚህ አሰዛኝ ሁኔታዎች እንድከሰቱ እያደረገ ያለዉ መንግስት በቃልም ይሁን በድርጊቶቹ፣ በተለያዩ ጽሑፎችና ሚዲያዎች፣ እንዲሁም በተለያየ መልክ እያካሄዳቸዉ ያለ (የሕዝቡ ቁስል ከመዳን ይልቅ እንዲያመረቅዝ የሚያደርጉ) እንቅስቃሴዎቹ ናቸዉ። ስለሆነም እነዚህ ሁኔታዎች እስካሁን ላደረሱት ጉዳቶችና ቶሎ ሳይታረሙ ቀርቶ ሊያደርሱ ለሚችሉትም ጉዳቶች ሁሉ ተጠያቂዉ መንግስት እራሱ መሆኑን እናሳስባለን። ኣሁንም ብሆን ለነዚህ ችግሮችና የሰላም እጦት ሁሉ ብቸኛዉ መፍትሄ የሕዝቦች ጥያቄ፣ ሀሳባቸዉና ፍላጎታቸዉ በአግባቡ ተደምጦ የተሟላና ቀና ምላሽ እንድሰጥባቸዉ ማድረግ ብቻ መሆኑን በአጽንዖት እንገልጻለን።
ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
ጥቅምት 12 2012 ዓ.ም.