የቅንጣቢ አካሄድ የመዋቅር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኢ-ፍትሃዊነትን ማስወገድ አይችልም።

 

የቅንጣቢ አካሄድ የመዋቅር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኢ-ፍትሃዊነትን ማስወገድ አይችልም።

የሳፋሪኮም ኢ-ፍትሃዊ ፖሊሲን በተመለከተ ከኦነግ የተሰጠ መግለጫ

የሰራተኞች ቅጥርን በተመለከተ ሳፋሪኮም በቅርቡ የወሰደው እርምጃ የፍትሃዊነት ጉድለት እንዳለው በግልጽ አሳይቷል። ይህን ኢ-ፍትሃዊነት በመቃወምም ኦሮሞዎች ግንባር ቀደም ሆነው የተሳተፉባቸው ከፍተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን አስነስቷል። ኦነግ ሁሉንም አይነት ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች በመቃወም የሚሰማ ድምጽና የሚደረግ እንቅስቃሴን ያበረታታል። ኦነግ ማንኛውንም አይነት ግፍ ያወግዛል።

እኩል የሥራ ዕድል የማግኘት መብት የኢኮኖሚ ነፃነት አንዱ ምዕራፍ ነው። በሳፋሪኮም የሰራተኞች ቅጥር ሂደት ውስጥ ያለው ኢ-ፍትሃዊነት እስካሁን ግልጽ ያልሆነውና አሁን ኢፋ የወጣው ለምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። አሁንም የኦሮሞን ቁስል እንደገና የሸነቆረ ሌላ ክስተት ሆኗል።

ነገር ግን ይህ የኦሮሞ ወጣቶች በሰፊው የኦሮሞ ፖለቲካና ኢኮኖሚ መብቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ይህን በመሰለው ቅንጣቢ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ የለበትም። ኦሮሞዎች ከመቶ ዓመት በላይ እንደኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮም ከመሳሰሉ ዋና ዋናዎቹ ተቋማትና ኩባኒያዎች እንዲሁም ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንደአስመጪና ላኪ፣ ሪልስቴት፣ ኢንደስትሪና የሀገር ውስጥ የንግድ ዘርፎች ስልታዊ በሆነ መንገድ ተገልለው ቆይተዋል። ይህንንም የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በፌደራል ፓርላማ ፊት አረጋግጠዋል።

በሣፋሪኮም የተፈፀመው ኦሮሞን ስልታዊ በሆነ መንገድ የማገለል አንዱ ማሳያ ሲሆን ይህንንም ድርጊት የሳፋሪኮም ተግባር ብቻ አድርጎ ማቅረብ፡ የኦሮሞ ወጣቶች ሁለንተናዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነትን ለማስፈን የሚደርጉትን ትግል አቅጣጫ ለማስቀየር የተደረገ ሴራ ነው። ይህም ኦሮሞን ስልታዊ በሆነ መንገድ ማገለሉ ጥልቅና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ ስር ከመስደዱ የተነሳ አለምአቀፍ ኩባንያዎች እንኳ የተዘረጋውን ኣግላይ ስርዓት እንዲኮርጁ ለማድረጉ ሌላው ማረጋገጫ ነው።

ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን ጨምሮ የኢኮኖሚ መዋቅሮች፡ ጨቋኝ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓቶችን በሚወክልና በሚደግፍ መንግሥት እስከተደገፉ ድረስ፣ የተለመደውን የፍትሕ መጓደልና የመገለል ስርዓት እንዲቀጥል ማሳያ ነው። ይህ ድራማ የፖለቲካ ትርፍ ለማግበስበስ ባሰበ እና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‘ጉዳዩ እልባት አግኝቷል’ በሚለን ቡድን የተቀነባበረ ነው ብለን እናምናለን።

የኦሮሞን ጥቅም ለማስጠበቅ የተነደፉትን ህጎች ለሚያከብርና ለምያስከብር በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጠ መንግስት መታገል ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን መላው ኦሮሞ ህዝብ በተለይም የኦሮሞ ወጣቶች መገንዘብ ኣለባቸው። የቅንጣቢ አካሄድ የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየርና መዋቅራዊና የስርዓት ችግር ያለባቸውን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ተቋማትንና የመንግስት አካላትን እድሜ ለማራዘም ያለመ ነው።

 

ድል ለሰፊው ህዝብ!

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር

ነሐሴ 17ቀን 2022ዓም