የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ

 

 

ABO Oromoo Gadaa Wareegamtoota

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ
ሰኔ 21, 2011 ዓም

ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከ43 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፊንፊኔ ከተማ ዉስጥ ጠቅላላ ጉባዔዉን ኣካሄደ። የኦነግ መስራች ጉባዔ በፊንፊኔ/አድስ አበባ ከተማ ዉስጥ ከተካሄደበት ከ1976 እ.ኤ.አ. ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደዉ ይህ ታሪካዊ ጉባዔ ድርጅቱን (ኦነግን) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብ ያቀደ ጉባዔ ነዉ። ይህ ጉባዔ በፊንፊኔ ጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ የኦነግ ዋና ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታዛቢነት በተገኘበት ነዉ የተካሄደዉ። ሰኔ 21, 2011 ዓም የተካሄደዉ ይህ ጉባዔ እንደሚከተለዉ የአቋም መግለጫ በማዉጣት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ።

እኛ ከኦሮሚያና ከሌሎችም የክልል መንግስታት የተላያዩ ዞኖች ተወክለን በፊንፊኔ/አድስ አበባ ሰኔ 21, 2011 ጠቅላላ ጉባዔያችንን ያካሄድን የኦነግ አባላት ተወካዮች የሚከተሉትን ዉሳኔዎችና የአቋም መግለጫን በማዉጣት ጉባዔያችንን እጅግ ባማረ ሁኔታ ኣጠናቀናል።

1. በኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንቡ ላይ በሰፊዉ ተወያይተን ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የሚጣጣሙ ማሻሻያዎችን ካደረግንበት በኋላ ኣጽድቀናል።
2. እስከሚቀጥለዉ ጠቅላላ ጉባዔያችን ድርጅታችንን፣ እንድሁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉን የሚመሩልንና የሚያስተባብሩልን አመራሮችን መርጠናል።
3. በተመሳሳይ መልኩ እስከሚቀጥለዉ ጠቅላላ ጉባዔያችን የድርጅታችንን ህገ-ደንብ፣ ስነ-ስርዓትና ስነ-ምግባር፣ እንድሁም የንብረት አያያዝን በተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ አስፈላጊዉን ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ የስነ-ስርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴንም መርጠናል።
4. ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉ የተሳካ ይሁን ዘንድ ድርጅታችን ከተለያዩ ሕዝባዊ ድርጅቶች ጋር እየፈጠረ ስላለዉ ትብብርና ትስስር አድናቆታችንን እየገለጽን ይህ ዓይነቱ ተግባር የበለጠ ተጠናክሮ እንድቀጥል ወስነናል።
5. ከመንግስት ጋር ባደረግነዉ የስምምነት ቃል ጸንተን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የኦሮሞና የሌሎችም ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትና ሌሎችም ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንድረጋገጡ፣ ኣልፎ ተርፎም ዘላቂ ሰላም እንድሰፍን የበለጠ ጠንክረን ለመስራት ወስነናል።
6. ሕዝባችን የከፈላቸዉንና እየከፈለም ያለዉን ከባድ መስዋዕትነት ፍረያማ ለማድረግ ዛሬም ብሆን ሰላማዊ ትግሉም የሚጠይቀዉን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለን ከግባችን በመድረስ በዚህች ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቃላችንን እናድሳለን።
7. በዚህች ሀገር ለነበሩና ኣሁንም ለሚስተዋሉት ፖለቲካዊ ችግሮች በሰላማዊና እዉነተኛ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ካልሆነ በስተቀር በጠመንጃ ኣፈሙዝ ዘላቂ መፍትሄ ማስገኘት ስለማይቻል ሁሉም የፖለቲካ ሓይሎች በጋራ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ስልቱን ማበረታታት እንዳለባቸዉ እናሳስባለን።

ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !
የኦነግ ጠቅላላ ጉባዔ
ሰኔ 21, 2011 ዓም