በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ልደረግበት ይገባል !

በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ልደረግበት ይገባል !

(የኦነግ መግለጫ – ጥር 23, 2012 ዓ.ም.)

Obsi ከምዕራብ ኦሮሚያ (የወለጋ ዞኖች) ቴሌፎንና ኢንተርኔትን የመሳሰሉት የመገናኛ አገልግሎቶች በመንግስት ከተቋረጡ 1 ወር ኣለፈ። ከዚህም የተነሳ የዕለት ተዕለት ክስተቶችን በጊዜዉ ከነበቂ መረጃ ጋር ማግኘት አዳጋች ብሆንም እንኳ የመንግስት ወታደሮችና ታጣቂዎች በሰላማዊ (ትጥቅ-ኣልባ) ዜጎች ላይ እያካሄዱ ባሉት ግድያ የሰዎች ህይወት እንደቅጠል እየረገፈ መሆኑ መተለያየ መንገድ እየተሰማ ነዉ። በተለይም በሁለት ዞኖች (ምዕራብ ወለጋ እና ቄሌም ወለጋ) ዉስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች በሕዝቡ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ግድያና ጭፍጨፋ በቃላት መግለጽ እንኳን ይከብዳል። የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የጦር ወንጀል የሚሉት ቃላቶችም በትክክልና በበቂ ሁኔታ ልገልጹት ኣይችሉም። በደቡብ ኦሮሚያ (በጉጂ ዞኖች) ያለዉ ሁኔታም እምብዛም ከዚህ የተለየ አይደለም። በዚህ መልኩ ከአንድ ዓመት በላይ በወታደራዊ አስተዳደር (ኮማንድ ፖስት) ሥር በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለዉን እሮሮና ስቃይ በተለያዩ ጊዜያት ገልጸን መፍትሄ እንድፈለግለት ብንወተዉትም እስካሁን የሕዝባችን ኡኡታና ችግሩ ተገቢዉን ተሰሚነት ሊያገኝ አልቻለም።

ባሁኑ ጊዜ በተጠቀሱት ቦታዎች በተለይና በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ባጠቃላይ በሰላማዊ (ትጥቅ-ኣልባ) ዜጎች ላይ የሚፈጸም ግድያና ጭፍጨፋ፣ የጅምላ እስር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ መባረር፣ ባጠቃላይ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣና የጦር ወንጀል (War Crime) ከመቼዉም ጊዜ ባላይ ዘግናኝና ከባድ ሆኗል። በነፃና ገለልተኛ አካል የሚደረግ ምርመራ፣ እንዲሁም አስቸኳይ መፍትሄ የሚፈልግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነዉ ብለንም እናምናለን።

ሆን ተብሎ በዶ/ር አብይ አህመድ በሚመራዉ የኢትዮጵያ መንግስት በሰላማዊ ሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለዉን ይህንን እሮሮና ሰቆቃን እጅግ ኣጥብቀን እናወግዛለን። ይህ እሮሮና መከራ ባስቸኳይ እንድቆምም አበክረን እንጠይቃለን። ይህ ችግር ባስቸኳይ ካልተገታ በስተቀር ከዚህም ወደባሰ ሁኔታ ኣድጎ ከማንም ቁጥጥር ዉጪ ልሆን እንደሚችል ስጋታችን እየጨመረ መሆኑንም ኣሁንም በዲጋሚ ኣስረግጠን ልንገልጽ እንወዳለን። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የህይወት መጥፋትና የንብረት ዉድመትን ጨምሮ እስካሁን ለደረሱትና በቃጣይም ልደርሱ ለሚችሉት ጉዳቶች ሁሉ ተጠያቂዉ የኢትዮጵያ መንግስት (የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር) መሆኑንም ግልጽ እናደርጋለን።

በመጨረሻም መፍትሄ ይሁን ዘንድ የሚከተሉት እርምጃዎች እንድወሰዱ ኦነግ በኣፅንኦት ይጠይቃል፡

  1. በግድያና ጭፍጨፋ፣ በእስራት እና በማንኛዉም መልኩ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በመንግስት እየተካሄደ ያለዉ ይህ እሮሮና ማሰቃየት ባስቸኳይ እንድቆምና ይህንን እያካሄዱ ያሉት የመንግስት ኃይሎች (ወታደሮች) ወደ ካምፕ እንድመለሱ።
  2. ያሉት ችግሮች በዉይይትና በሰላም መፍትሄ የሚያገኙበትን ሁኔታ መንግስት እንዲያመቻች።
  3. ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸዉ እና ቀዬአቸዉን ለቆ ለመሸሽ የተገደዱ ሰዎች ወደ ቀዬአቸዉ ተመልሶ ስላማይ ኑሮዋቸዉን እንድኖሩ፣ ከደረሰባቸዉ ጉዳት የሚያገግሙበት እገዛም እንድደረግላቸዉ። ያለምንም ጥፋትና ህጋዊ ዉሳኔ በተለያዩ ቦታዎች የታሠሩት እንዲፈቱ እና በኢፍትሃዊ መንገድና በተለያዩ ሴራዎች ከትምህርት ገበታቸዉ የተለዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸዉ የሚመለሱበት ሁኔታ ባስቸኳይ ተመቻችቶላቸዉ እንድመለሱ እንዲደረግ።
  4. በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተፈጸመ ያለዉን ግፍና ሰቆቃ፣ በዚህም እየደረሰ ያለዉን ጉዳት በተመለከተ በነፃና ገለልተኛ አካል አስፈላጊዉ ምርመራ ((International Investigation) እንዲደረግበት።

ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
ጥር 23, 2012 ዓ.ም.