የብልጽግና ፓርቲ በኦሮሞ ህዝብ እና በኦሮሚያ ዘጎች ላይ የወጣውን ዘርፈ ብዙ ጦርነት አስመልክቶ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ የኦነግ መግለጫ- ሚያዚያ 21፣ 2014

 

የብልጽግና ፓርቲ በኦሮሞ ህዝብ እና በኦሮሚያ ዘጎች ላይ የወጣውን ዘርፈ ብዙ ጦርነት አስመልክቶ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ የኦነግ መግለጫ- ሚያዚያ 21፣ 2014

በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ በኦሮሞ ህዝብ እና በኦሮሚያ ዜጎች ላይ የማያቋርጥ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል። በአሁን ወቅት የኦሮሞ ህዝብ ለገዢው ፓርቲ እንዲገዛ እና አሮጌው የቅኝ ግዛት ፕሮጄክት እንዲያንሰራራ ለማድረግ ገዢው ፓርቲ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ዘርፈ ብዙ እና ከመቸውም ጊዜ በላይ የእያንዳንዱን ኦሮሞ ህይወት ከባድ ለማድረግ ፣ እንዲሁም የኦሮሞ ተቋማትን ለማዳከም እና በአጠቃላይ ኦሮሚያን ለማፍረስ የታለመ ነው። የዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ኦሮሞነትን ለማጥፋት፣ ኦሮሞነትን ለማፍረስ እና የኦሮሞን ህዝብ ለማዳከም የታቀደ ስልታዊ ስትራቴጂ በመተግበር ላይ ይገኛል። የአምባገነኑ ብልጽግና ዘመቻዎች የኦሮሞ ህዝብ እና ሌሎች ብሄሮች እና ብሄረሰቦች የዳግማዊ ምኒልክ ፕሮጄክት በማንሰራራት መርህ ለአፄዎች ገዥ መደብ ስርዓት እንዲገዙ ማስገደድ ነው። ዘመቻውም ብሔርን እና ፓለታካዊ አስተሳሰብ መሰረት ባደረገ መልኩ መሬት በመንጠቅ ስልታዊ ድህነትን መፍጠር፣ ተስፋፊውን ቡድን የኦሮሞን መሬት እንዲወስድ መደገፍ፣ ብሄርን መሰረት ያደረገ ግድያና ማፈናቀል፣ በብልጽግና ታጣቂ ሃይሎች የጸጥታ አባላት ጉቦ እና ሙስናን ያካትታል። በዚህ ረገድ የኦሮሞ ህዝብ በዘር ላይ የተመሰረተ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ ድህነት እና የዕለት ተዕለት እንግልት፣ መፈናቀል እና ለተለያዩ ግጭቶች ተጋልጧል። የብልጽግና መንግስት በህዝቦች መካከል ግጭቶችን በመቀስቀስ የህዝቦችን ሰላማዊ አብሮነት በመሸርሸር በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል አለመረጋጋት እየፈጠረ ነው። የብልጽግና አገዛዝ ሆን ብሎ ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ ከማድረግ ባለፈ የግለሰቦችን የእምነት፣ የማንነት፣ የትምህርት እና የማህበራዊ ትስስርን ጨምሮ የግለሰቦችን መሰረታዊ መብቶች በመግፈፍ ላይ ነው። ሰሞኑን በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙው ጭቁኑ የሙስሊም ማህበረሰብ ላይ በመንግስት በሚደገፍ አሸባሪ ቡድን የደረሰው ጥቃት መንግስት በሃይማኖታቸው ምክንያት የሀይማኖት ገለልተኝ ነት ከቶ አለመኖሩን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ይህም የገዥው ሥርዓት አባል ያልሆኑ ቡድኖችን የሃይማኖት ነጻነት በግልጽ ይጋፋል። የትምህርት ሥርዓት፣ የልማት ፕሮግራሞች እና የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ እኩልነት አለመኖሩን በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ኦሮሞን ማዋከብ እና የኦሮሞ እና የሌሎች ጭቁን ህዝቦችን የፖለቲካ እና ማህበራዊ ተቋማትን ለማዳከም መሞከር ሌላው ዲሞክራሲን ለመናድ እና በተጨቆኑ ህዝቦች ላይ አምባገነናዊ ዘውዳዊ ስርአት ለመጫን የሚደረገው ጥረት ዋናው ማሳያ ነው። በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ እና የኦሮሚያ ዜጎች በክልሉ እየደረሰ ባለው ወከባ እና ሰላምና መረጋጋት እጦት የእለት ተእለት ስራቸውን ማከናወን ተስኗቸዋል። በኦሮሞ ህዝብ ላይ የታወጀው ወታደራዊ ዘመቻ ከምንጊዜውም በላይ መጠነ ሰፊ እና አሰቃቂ ነው። ሚያዚያ 13 ቀን 2014 የብልጽግና መንግስት እና የአማራ ክልል መንግስት በወሎ ኦሮሞዎች ላይ ከፍተኛ እልቂት ያደረሰውን የሰላማዊ ዜጎች ጭፍጨፋ አስመልክቶ መግለጫ ማውጣታችን ይታወሳል። አሁንም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በማዕከላዊ ኦሮሚያ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በምስራቅ ወለጋ እና በጉጂ ዞኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የብልጽግና አገዛዝ የፈፀመውን አሰቃቂ ወንጀሎች ለህዝብ ስናሳውቅ በሃዘን ነው። ዝርዝሩ እንደሚከተለው ነው። 1. ሚያዚያ 18 ቀን 2014 በማዕከላዊ ኦሮሚያ በአዳአ ባርጋአ ወረዳ የአገዛዙ ታጣቂ ሃይሎች የ70 አመት አዛውንትን ጨምሮ 15 የኦሮሞ ተወላጆችን ገድለዋል። ታጣቂዎቹ ገንዘብ፣ ጌጣጌጥ፣ የቤት እቃ ዘርፈዋል። የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን እያቃጥለዋል። ህጻናትና አረጋውያን ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ጫካ እየሸሹ ይገኛሉ። የተጎጂዎችን ዝርዝር ፍላጎት ላላቸው አካላት እናቀርባለን። 2. ሚያዚያ 20 ቀን 2014 የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በምዕራብ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ዲጋሉ፣ ጢጆ፣ ጢዮ፣ ሄጦሳ፣ ኢታያ፣ ሙኔሳ፣ ሊሙኡ ሂልቢሎ፣ ቦቅቆጂ፣ ሮቤ እና ዝዋይ ዱግዳን ጨምሮ ከ31 በላይ የሚሆኑ የኦሮሞ ተወላጆችን በጅምላ አስረዋል። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሲቪል እስረኞች በተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው በአገዛዙ ታጣቂ ሃይሎች እየተሰቃዩ ይገኛሉ። በዚህ ሳያበቃ የአገዛዙ ታጣቂ ሃይሎችም እስረኞቹ 20,000-30,000 ብር በነፍስ ወከፍ እንዲከፍሉ የሚያዙ ቢሆንም ከእስር ለመለቀቃቸው ግን ዋስትና አይሆንም። በተጨማሪም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን ፈልገው ለጸጥታ ሀይሎች የማያቀርቡ ከሆነ እርሻቸውን እንዳያርሱ እንደሚከለከሉና ካስፈለገም መሬታቸውን እንደሚነጠቁ ዛቻ ይደርስባቸዋል። 3. ሚያዚያ 18 ቀን 2014 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን (ፊንጫ) ሶስት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 3ቱ ጠፍተዋል። በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ ዞን (ኪራሙ ወረዳ) የቀብሪዳሃር ዩኒቨርሲቲ አንድ ተማሪ በመንግስት ታጣቂዎች ተገድሏል። ከዚህ ቀደም በሚያዚያ 8 ቀን 2014 በሆሮ ጉዱሩ ዞን (ኪራሙ) 36 የኦሮሞ ዜጎች

በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች ተገድለዋል። 4. በዚህ ሳምንት በሰሜን ምስራቅ ፊንፊኔ እና ሰላሌ ዞን (አቦቴ፣ ሀሮ፣ ኩዩ፣ ሜታ እና ግንዳበረት) በአየር ጥቃት ጨምሮ ከ30 በላይ ንፁሀን ዜጎች ተገድለዋል። 5. ሚያዚያ 15-17 /2014 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ (አምቦ እና አካባቢው) 19 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። 6. ሚያዚያ 20 ቀን 2014 በጉጂ ዞን (ቡሌ ሆራ ወረዳ) 11 ሰላማዊ ሰዎች በጅምላ ተገድለዋል። 7. ከብዙ በጥቂቱ ይህን ያህል ብንጠቅስም በኦሮሞ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ በመላው ኦሮሚያ በስፋት እንደቀጠለ ነው። ኦነግ ይህንን ዘርፈ ብዙ ጦርነት በኦሮሞ ንፁሀን ዜጎች እና በኦሮሚያ ዜጎች ላይ በፅኑ ያወግዛል፣ በምዕራብ አርሲ እና በማዕከላዊ ኦሮሚያ የታሰሩ ሰላማዊ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንድሁም፣ የተወረሱ ንብረቶቻቸው እንዲመለሱ እና ለተቃጠሉት ቤቶችና ለንብረት ውድመት ካሳ እንዲከፈላቸው ይጠይቃል። የኦሮሞ ህዝብ በጦርነት እና በግጭት ለዘውዳዊ ስርአት እንዲገዛ ማድረግ እንደማይቻል ለብልጽግና መንግሥት ማስታወስ እንፈልጋለን ። በኦሮሞ ህዝብ እና በኦሮሚያ ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ወንጀል ከመቀጠል ይልቅ ገዥው ቡድን በኢትዮጵያ ለዘመናት ለዘለቀው የፖለቲካ ቀውሶች በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲፈልግ እናሳስባለን። በንጹሃን ዜጎች ላይ ግጭቶችና ደም መፋሰስ መባባስ ሰላምና መረጋጋትን እንደማያመጣ ይልቁንም መከፋፈልንና መበታተንን እንደሚያጠናክር ገዥው ቡድን ሊያውቅ ይገባል። እንዲሁም የአንድ ፓርቲ – የአንድ ሃይማኖት – የአንድ ሀገር ገዥ ስርዓት አባዜ በማያቋርጥ ወታደራዊ ዘመቻ እና አሸባሪ ቡድኖችን ወደ ኦሮሚያ በማሰማራት እና በኢትዮጵያ ውስጥ የተጨቆኑ ብሔር ብሔረሰቦችን መብቶች በመናድ የተሳካ አይሆንም። አሁን በኦሮሚያ እየደረሰው ላለው ግድያና ውድመትና ወደፊትም በኢትዮጵያ ላይ ለሚኖረው መዘዞች የገዢው መንግስት ተጠያቂ ነው። ኦነግ አሁንም በኦሮሚያ ውስጥ ላለው አለመረጋጋት ግጭቶችን ከማስፋት ይልቅ በኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላም፣ ደህንነት እና አብሮ መኖር ላይ ከፍተኛ መዘዝ ስለሚያስከትል፣ የታጠቁ የጎረቤትና ባዕድ ሃይሎች ከኦሮሚያ እንዲወጡና፣ ትጥቃቸውን አስቀምጠው በሰላማዊ የፖለቲካ ድርድር ሂደት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሰሩ እናሳስባለን።

በመጨረሻም ለኦሮሞ ህዝብ ደግመን ማስታወስ የምንፈልገው ይህ ጊዜ ለእናንተ የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው፣ እራሳችሁን እና ማንነታችሁን በህብረት መከላከል አለባችሁ። ከሌሎች ብሄሮችና ህዝቦች ጋር በመተባበር ለነጻነትና ለዲሞክራሲ መታገል ይጠበቅባቹሃል። እንዲሁም ሰፊው የኦሮሞ ማህበረሰብ እና በአገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የኦሮሚያ ዜጎች በኦሮሚያ ከሚገኙ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የቁሳቁስ ድጋፍ እና ድምጻቸውን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሰሙ በማድረግ በምዕራብ አርሲ፣አዳአ በርጋ፣ግንዳበራት፣ሆሮ ጉዱሩ የሚገኙ የኦሮሞ ህዝብ እና የኦሮሚያ ዜጎች ከጎናቸው እንዲቆሙ። በተጨማሪም የተጨቆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ከኦሮሞ ሕዝብና ከኦሮሚያ ዜጎች ጋር እድትታባበሩ እናሳስባለን። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የገዥው ፓርቲ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በንጹሐን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል እና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲያቆም እንጠይቃለን። እንዲሁም መንግስታትን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን፣ የአፍሪካ ህብረትን፣ የአውሮፓ ህብረትን እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሰብአዊና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብአዊነት ላይ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠብ እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውሶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጫና እንዲያደርጉ እናሳስባለን።

ድል ለሰፊው ህዝብ!

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ

ሚያዚያ 21, 2014 ፊንፊኔ