የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግሮችና መሰረታዊ መፍትሄው

Obsi

 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግሮችና መሰረታዊ መፍትሄው

(Civil Political Discourse for Ethiopian Peoples)

 

ኢትዮጵያ በኣሁኑ ወቅት የገባችበት የፖለቲካ ችግር በተለይም ደግሞ በኦሮሚያ እየታዩ ያሉት ውስብስብ ችግሮች ኦሮሚያን የቀውስና ጦርነት ኣውድማ በማድረግ ኣለመረጋጋት እንዲኖር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከማትወጣበት ጥፋት እየዘፈቃት ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ኣስተዳደር ስር ይገኛል። የፖለቲካ ችግር በወቅቱ ባለመፈታቱ የተነሳ የቀድሞው የመንግስት መዋቅር ተበጣጥሷል። በኣሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ውስጥ የህዝቡን ችግር የሚፈታ የተመረጠ የአስተዳደር ኣካል የለም። ህዝቡ ሲገደል፣ ሲዘረፍ፣ ንብረቱ ሲወድምበት ስሞታውን ኣቅርቦ መፍትሄ የሚያገኝበት ቦታ ኣጥቷል። ይህ እንዲሁ ከቀጠለ ከዚህ የባሰ ኣስከፊ ችግር ሊከተል ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ኣካላት መንቀሳቀስ ለኦሮሚያ መፈራረስና ልንወጣው ከማንችለውና ኋላም እንዴት መያዝ እንደሚቻል ወደማናውቀው ችግር ይከተናል።

 

የኦሮሚያ መፈራረስ የኦሮሞን ህዝብ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ ዜጎች ላይ የማያቋርጥ ችግር ማስከተሉ ይታወቃል። ከግለሰብ ኣንስቶ እስከቤተሰብና ሃገር ድረስ በኢትዮጵያ ከባድ እየመጣ መሆኑን ማንም ሊክደው ኣይችልም። ስለሆነም ኣስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ለማስገኘት ኣስቸኳይ መፍትሄ ማፈላለጉ በእጅጉ ኣስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

 

ኦሮሞና የኦሮሚያ ዜጎች በርካታ ጉዳዮችን ይጋራሉ። ኣንድ ሃገር፣ ኣንድ የኑሮ ሁኔታ፣ ተመሳሳይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮችና ባህልን መጋራታቸው ለረጅም ዓመታት የነበረ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ያመጣብንን ሁሉንም ችግር ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግሮ ኣብረን ስንታገላቸው እንደነበርንና ኣሁንም በመታገል ላይ እንዳለን ይታወቃል። ይህም ኦሮሞ ከሌሎች ዜጎች ጋር ያለው ግንኙነት ይበልጥ ጠንካራ መሆኑን እያሳየ ነው።

 

ካሁን ቀደም በበርካታ ትግል ውስጥ ኣብረን ኣሳልፈን እዚህ እንደደረስነው፡ ኣሁንም ኦሮሞና የኦሮሚያ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘን ኣብረን በመስራት የጋራ የሽግግር መንግስት በመመስረት ከዚህ ችግር ለመውጣትና በጋራና በየግል ያለንን ዓላማ የምናሳካበት ጊዜ ኣሁን ነው ብለን እናምናለን። ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የኦሮሚያ ክልልን በማረጋጋቱ ረገድ የበኩላችሁን ድርሻ በመወጣት በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖረውን ዜጋችሁን መታደግ ብቻ ሳይሆን እንደሃገር በጋራ ያለንን መሰረት ለማድረግ ይረዳላን የሚል እምነት ኣለን።

 

የኦሮሚያ መፈራረስ የሚያስከትለው ችግር በእጅጉ ሰፊ ነው። ችግሩ የኦሮሞና የኦሮሚያ ዜጎች ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ችግር እንደሆነ መገንዘብ ኣለብን።

ስለሆነም ኣሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ የኦሮሚያ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት በኣስቸኳይ መመስረት ወሳኝ ሆኖ ተገኝቷል። መረዳት ያለብን ቢኖር የሽግግር መንግስት መመስረቱ ሃገርን ለማፈርረስ ሳይሆን ከመፈራረስ ለመታደግ፣ ከተጋረጠው ኣደጋ ሃገሪቷንና የኣፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማዳን መሆኑን ለኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ለኣፍሪካ ቀንድ ሃገራትና ለኣፍሪካ ኣህጉር እንዲሁም ለኣለም መንግስታት ማረጋገጥ እንሻለን።

 

በታሪክ ኦሮሞ ሃገር ኣፍርሶ ኣያውቅም፡ ይገነባል እንጂ፣ ኦሮሞ ለራሱ ብቻ ኣስቦም ኣያውቅም ብሄር ብሄረሰቦችን ኣሰባስቦ ኣብሮ መኖር እንጂ። ለዚህም ዋነኛው ምስክር ከኢትዮጵያ ውስጥ ከሁሉም በላይ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን በብዛት ያቀፈው ኦሮሚያ መሆኑ ነው። ስለዚህ ኦሮሚያ በርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የሚገኙባት ኢትዮጵያ ተምሳሌት ነው ለማለት እንችላለን። የሽግግር መንግስት ማቋቋሙ በኦሮሚያ ውስጥ ለሚኖሩ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ኣንድነታቸውንና ኣብሮ መኖራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ኣስፈላጊ ነው። በመሆኑም ይህ የሽግግር መንግስት በታሪክና በባህል የተገነባውን ይበልጥ ለማጠናከር እንጂ ጥፋትና መፈራረስን ለመፍጠር እንዳልሆነ በድጋሚ ማረጋገጥ እንሻለን። በኦሮሞና በሌሎች የኦሮሚያ ዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ ፍቅርን ለማጎልበትና ኣብረን ሃገር በመመስረት ላይ በመመርኮዝ ኣብረን መጓዝ እንሻለን። ይህ ለሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችም የኣስተማማኝ ሰላም መሰረት ይሆናል ብለን እናምናለን።

 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦሮሞና ሌሎችም የኦሮሚያ ዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮኣችሁን እየጎዳ ያለውን ውስብስብ ችግር ኣብረን ልንፈታ እንችል ዘንድ ጥሪውን ያቀርብላችኋል። ለመላው ኦሮሞና የኦሮሚያ ዜጎች እያቀረብን ያለው ይህ ጥሪ በኣሁኑ ወቅት የሚመሰረተው የሽግግር መንግስትም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከህዝቡ፣ በህዝቡ ህዝብን ለማገልገል የተመረጠ መንግስት(government of the people by the people for the people) ለማቋቋም ወሳኝ መሰረት የምንጥልበትና ሁኔታ የምናመቻችበት ጊዜ ነው። መጻዒያችን ትንሽ ትልቅ ብሎ ሳይለይ ሁሉም የኦሮሚያ ዜጎች ድምጻቸው ዋጋ የሚገኝበት እንደሚሆን እርግጥ ነው።

 

ዓላማችንና የሽግግር መንግስቱ ግብ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ኣድልዖኣዊ የፖለቲካ ባህል(partisan political culture) ቀይረን በህዝቡ ተመርጦ ህዝቡን በሚያገለግል ሁሉንም የኦሮሚያ ዜጎች ያቀፈ መንግስት ለመተካት መሆኑን ማረጋገጥ እንሻለን።

 

ኦነግ የፖለቲካ ዓላማውን ሰው ላይ የሚጭን ሳይሆን የተለያዩ ኣካላትን ኣድምጦ ለሁሉም ዜጎች በሚሆን መልኩ የጋራ የኣስተዳደር ኣካል በመመስረቱ ላይ ጥረት ያደርጋል። ይህንንም እውን ለማድረግ መሰረቱን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ከሁሉም የኦሮሚያ ዜጎች ጋር ኣብረን እንድናበጅ ማሳሰብ እንወዳለን። ይህም ለሁላችንም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ያስገኛል ብለን እናምናለን።

 

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ቀይረን በኦሮሚያ ላይ ኣስተማማኝ መረጋጋት ያለበት፣ ሁሉን ያቀፈ፣ ሁሉንም የሚያከብርና እኩል የሚያገለግል መንግስት ከመሰረትን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሃገራችን ምን እንደምትመስል ሁላችንም መገመት እንችላለን።

በዜጎች እኩልነትና በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መንግስት ከተቋቋመ፣ ግልጽ የሆነ የብሄራዊና የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ካለ፣ ህግ ኣውጪና ህግ ኣስፈጻሚው ኣካል ተለይቶ ከተቋቋመ፣ ሰላምን የሚያስጠብቅና ሃገርን የሚከላከል ኣካል ስልጣን ላይ ባሉ ኣካላት የማይነዳ ከሆነ፣ መንግስት ለፈጸመው ጥፋት ሃላፊነት ካለው፣ ሰብዓቂ መብት እንደግለሰብና በጋራ ከተከበረ ሃገር ዜጎቿ በሰላምና በደስታ የሚኖሩባት ትሆናለች ብለን እናምናለን።

 

ሰላምና መረጋጋት ካለ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ይህ ሃገር የኔ ነው፣ ይህ የኔ መንግስት ነው ብለው ካመኑ እድገትና ብልጽግና ማምጣት ኣያስቸግርም። ሃገራችን ለምና የኣለም ኢንቨስትመንትን የምትስብ ናት። ይሁን እንጂ ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ኢንቨስተሮች ይሸሹናል። የሃገር ውስጥም ይሁን የውጪ ባለሃብቶች ያለኣንዳች ስጋት እንዳሻቸው ኢንቨስት ማድረግና ሃገራችንን ከልመና ልናላቅቅ የምንችለው ሰላምና ኣስተማማኝ መሰረት ያለው መንግስት ሲኖር ብቻ ነው። ሰላምና የተረጋጋ ህዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት ሲኖር ብቻ ነው ወጣቶችና የተማረው ሃይል በስራ ሃገርን ወደ መለወጡ ሊሰማራ የሚችለው። ይህ ሲሆን ነው ሰው በሰላም ወጥቶ ሰርቶ ቤተሰቡን ማኖት የሚችለው፥ የግልና የጋራ ሃብት ዋስትና የሚያገኘው፣ ልጆቻችን በሰላም ወጥተው ተምረውና ሰርተው በሰላም ይገባሉ፣ ከጥላቻና ጦርነት ይልቅ ፍቅርና መተጋገዝ በህዝባችን መሃል ይሰፍናል። የመረዳዳትና መደጋገፍ ባህላችንንም መልሰን ልንገነባ እንችላለን።

 

በመጨረሻም በኣሁኑ ወቅት ሃገራችንን ያጋጠማት የፖለቲካ ችግር በእጅጉ ውስብስብ ነው። በበሰበሰውና ለበርካታ ዓመታት በዘለቀው የፖለቲካ ባህል ስር ይህን ውስብስብ የፖለቲካ ችግር መፍታት ኣልተቻለም። ኣያሌ ጊዜያት ተሞክሮ፣ በርካታ ህይወት ተከፍሎበት፣ በርካታ ሃብት ወድሞበት ኣልተሳካም። ይህንን ውስብስብ ችግር ተገናኝተን በመወያየት የመፍትሄ መንገድ ካበጀን ብቻ ነው ልንወጣው የምንችለው። ኣሁን ያለው ኣንዱና ብቸኛው የመፍትሄ መንገድ ለሌሎች መንግስታትና ክልሎችም የሰላም መሰረት የሚሆን ብሄራዊ የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት የኦሮሚያ ዜጎች በጋራ ማቋቋሙ ነው። ይህም የበኩላችንን ተሳትፎ የምናደርግበትና ፍላጎታችንን የምንገልጽበት ይሆናል። እንዲሁም ኣሁን ያለንበትን የሰላምና መረጋጋት ችግር መፍታት የምንችለው ተገናኝተን በመወያየት ብሄራዊ የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት ካቋቋምን ብቻ ይሆናል።

 

ኦነግ የሽግግር መንግስቱን ምስረታ ስራ ላይ ለማዋል ባለው ኣቅም ሁሉ ለስካታማነቱ በመስራት ላይ መሆኑን ያረጋግጣል። የህዝቡንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ኣካላትን ሃሳብ ወስደን ለህዝቡ በሚሆን መልኩ በጋራ ኣስተዳደር ለማቋቋም ሁሌም ዝግጁ መሆናችንን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኦሮሚያ ብሄራዊ ሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደትን በተመልከተ በተለያየ መንገድ ከናንተ ጋር ግንኙነት በመፈጠር ስራ ላይ በማዋሉ ኣብሮኣችሁ ተወያይቶ እንደሚሰራ ያረጋግጥላችኋል።

 

በመጨረሻም ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ለዲሞክራሲ መብት፣ የህዝቦች መብት እንዲከበርና ለብሄሮችና ብሄረሰቦች እኩልነት መረጋገጥ በመፋለሙ ላይ ህይወታቸውን ለሰዉ የኦሮሚያ ዜጎችና ለሌሎችም ብሄር ብሄረሰብ ዜጎች ሁሉ ያለኝን የላቀ ክብር መግለጽ እወዳለሁ። በተለይም ዘልዓለማዊ ክብር ለዚህ ላበቁን ታጋዮቻችን ይሁን።

 

እንዲሁም ሃገርን ለመታደግ፣ ከህዝቡ ጎን የቆሙና ሰላምን ለማውረድ ሲፋለሙ ህይወታቸውን ላጡ የደህንነት ሃይሎች ታላቅ ኣክብሮት ለመስጠት እወዳለሁ። በተለይ የሰብዓዊ ክብር ጠብቃችሁና ስራችሁን በህጉ ኣግባብ በማከናወን ኣሁን ባለው ኣስቸጋሪ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ቤተሰቦቻቸውንና ኑሮኣቸውን ትተው ሌትተቀን የህዝቡን ደህንነት በመጠበቅ ላይ ያሉትን የፊንፊኔ(ኣዲስ ኣበባ) ፖሊስና ደህንነት ሃይሎችን በእጅጉ አደንቃለሁ፥ ኣከብራለሁ።

 

እንዲሁ እንደግለሰብ፣ እንደቡድንና እንደተቋም ከጎናችን በመቆም ጽናታችንን ይበልጥ ኣጠንክረን ኣሁን ያለንበት ቦታ

እንደንደርስ ላደረጋችሁን ሁሉ ምስጋናዬን ኣቀርባለሁ።

 

ለኦሮሚያ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት መቋቋም ጥሪ ካቀረብን ወዲህ ጥሪውን ተቀብላችሁ ከጎናችን በመቆም ለስኬታማነቱ ከኛ ጋር የተሰለፋችሁትን ከዚህ በታች ያላችሁንም ላመሰግን እወዳለሁ፡

 

1. ይህንን ጥሪያችንን ተቀብላችሁ ከኛ ጋር የቆማችሁ የተከበራችሁ የኦሮሚያ ዜጎች

2. የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ኣጋራችን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ(ኦፌኮ)

3. በሃገር ቤትና በውጪ ሃገራት ለሚገኑ የኦነግ ኣማራር

4. በሃገር ቤትና በውጪ ሃገራት ለሚገኙ የኦነግ ኦፊሰሮች

5. ለቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ

6. ለደጋፊዎቻችንና ለኦሮሞ ማህበረሰብ

7. ለኦሮሞ ምሁራን ቡድን(The Oromo Scholars and Professional Group)

8. ለኦሮሞ ግሎባል ፎረም(Oromo Global Forum)

9. ለህዝባችን ድምጽ ለመሆን ጥሪ ላቀረባችሁ የተለያዩ ሃይማኖት መሪዎች

10. ለግሎባል ኦሮሚያ የጋዜጠኞች ማህበር(Global Oromiyaa Journalist Association)

11. ለአለም-ኣቀፍ የ39 ንቅናቄ ድጋፍ ቡድን

12. የኦሮሚያ ዜጎች የፖለቲካ እስረኞችን ለማስፈታት ተደራጅታችሁ እንቅስቃሴ ለጀመራችሁ የኦነግ ኣባላትና ደጋፊዎች ኮሚቴ

13. እንዲሁም ስማችሁ ያልተጠቀሰ ሁሉ

 

ስላዳመጣችሁኝ ኣመሰግናለሁ።

 

ድል ለሰፊው ህዝብ!

ዳዉድ ኢብሳ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ-መንበር

 

ጥቅምት 8, 2020ዓም

ፊንፊኔ(አዲስ ኣበባ), ኢትዮጵያ