ምላሽ ለኣፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መግለጫ

OLF

 

ምላሽ ለኣፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር መግለጫ

(የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ -ህዳር 4, 2020ዓም)

 

የኣፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ክቡር ሙሳ ፋኪ መሃሜት ህዳር 3, 2020ዓም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ኣስመልክተው ላወጡት መግለጫ ያለንን ታላቅ ኣድናቆት እንገልጻለን። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ያንሻበበውን አደጋ ኣስቀድሞ በመገመትና የለውጡ ሂደት መስመር እንዲይዝና በኣግባቡ እንዲመራ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ መንግስት ሲገልጽ ሰንብቷል።

ለቀውስና ለግጭቶች በጊዜ መፍትሄ እንዲበጅ ሃሳብ በማቅረብ ሁሉም ባለድርሻ ኣካላት በውይይትና ዲሞክራሲን እውን በማድረጉ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ሲጠይቅ ነበር። በተለይም የደህንነት ችግርና በማህበረስብ መካከል ያሉ ግጭቶችን አስመልክተን ያለንን ከፍተኛ ስጋት ገልጸናል።

 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በተናጠልና ከሌሎች ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር በጋራ በመሆን የለውጥ ሂደቱን መልክ በማስያዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር ያመራ ዘንድ ኣገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ ሁሉንኣቀፍ ብሄራዊ ውይይት እንዲካሄድ ሰፋ ያለ የመፍትሄ ሃሳብ በማርቀቅ ኣቅርቧል። ለውጡ በኣግባቡ ካልተመራና የተለያዩ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ላሏቸው ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሰረታዊና ፍትሃዊ ምላሽ ካልተሰጠ ሊከሰት የሚችለውን ከባድ ኣደጋ በተከታታይ ለዓለም ማህበረሰብ ሲያሳውቅ ነበር።

 

የኣፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ስጋታችንን ከትኩረት ውስጥ በማስገባትና በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ሁሉን ኣቀፍ ውይይት ለማካሄድ ጥረት መደረግ እንዳለበትና ሃገሪቷን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን በመግለጹ ኦነግ የተሰማውን ደስታ ይገልጻል።

በተደጋጋሚ ስንገልጽ እንደነበረው ላጋጠመው ህገ-መንግስታዊ ቀውስ መፍትሄ ለማርቀቅ፣ ኣስፈላጊውን ስትራቴጂ ለመቀየስና በስራ ላይም ለማዋል በሚደረግ የጋራ ጥረት ሁሉ ውስጥ በመሳተፍ ድርሻችንን ለማበርከት ያለንን ፍላጎት እንገልጻለን።

 

ክቡር ሊቀ-መንበር፡ በዚህ ኣጋጣሚ በመጠቀም ትኩረትዎን እንዲያገኝ የምንሽው ጉዳይ፡ በኢፌዴሪ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዜጎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኢፌዴሪ ውስጥ የኦሮሚያ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ያቀረበውን ጥሪ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ደግፈውታል።

ይህም ብዙ ህዝብ በሚኖርበት በዚህ ክልል ውስጥ የፖለቲካ ቀውስና የደህንነት ችግር ይበልጥ እንዳይከፋ ይረዳል ብለን እናምናለን። ከዚህም ሌላ የኦሮሚያ ብሄራዊ ሽግግር መንግስት መመስረት በቀጣይነት እየተፈጸመ ያለውን ግድያ፣ የጅምላ እስራት ይህንን ሰቆቃ ለማስቆም በተደጋጋሚ እየተካሄደ ላለው ኣመጽ ምላሽ በመሆን፡ በኢትዮጵያ ሰፊው ለሆነው ለዚህ ክልል የሰላም መስረት በመጣል መረጋጋትን ያሰፍናል የሚል ጽኑ እምነት ኣለን።

 

በመጨረሻም የኣፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሁሉም ኣካላት በሁሉን-ኣቀፍ ውይይት እንዲሳተፉ ያቀረበውን ጥሪ የምንቀበል መሆኑንና ኣገራዊ መግባባትን በመፍጠር ሃገሪቷ የገጠማትን ህገ-መንግስታዊ ቀውስና ይህም በኣፍሪካ ቀንድ ቀጣናና ከዚያም ባሻገር የሚያደርሰውን ከባድ ጫና ለማስቀረት ከሁሉም ባለድርሻ ኣካላት ጋር የሚሰራ መሆኑን ይገልጻል።

 

ድል ለሰፊው ህዝብ!

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር

ህዳር 4, 2020ዓም