የሲዳማ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ የሚወስደዉን ማንኛዉንም ዉሳኔ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ያከብራል

የሲዳማ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ የሚወስደዉን ማንኛዉንም ዉሳኔ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ያከብራል

(የኦነግ መግለጫ – ሓምሌ 08, 2011 ዓም)

adda ummataየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 3 ማንኛዉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረ-ሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዳለዉ ይደነግጋል። ይህ መብት ብሔሩ ወይም ሕዝቡ በሰፈረበት መልከአ-ምድር ዉስጥ ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማትን የማቋቋም፣ በክልልና በፌዴራል የአስተዳደር መዋቅሮች ዉስጥ ሚዛናዊ ዉክልና የማግኘት መብትን ይጨምራል።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀዝ 47 ንዑስ አንቀጽ 1 ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመስረት መሆኑን ይደነግጋል። በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ስር ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ሕዝቦች በማንኛዉም ጊዜ የራሳቸዉን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸዉ ተደንግገዋል። የክልል መመስረት ጥያቄ አፈጻጸምና ሂደትም በዝርዝር ተቀምጠዋል።

የሲዳማ ሕዝብ የብሔር ጥያቄ ኣንግበዉ ያራሳቸዉን ዕድል በራሳቸዉ ለመወሰን ለዘመናት ስታገሉ ከነበሩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረ-ሰቦች ኣንዱ መሆኑ ይታወቃል። በ1983 ዓም የደርግ መንግስትን ጥሎ የሽግግር መንግስት ከመሰረቱት የነፃነት ድርጅቶች ኣንዱ የሲዳማ ነፃነት ንቅናቄ እንደነበርም ይታወሳል። በ1984 የፌዴራል ስርዓት/መንግስት በ 13 ክልሎችና በመዲናዋ (ፊንፍኔ/አድስ አበባ) በአዋጅ ከተዋቀረ ጊዜ ጀምሮ በተለይም በ1987 የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ስጸድቅ በደቡብ የነበሩ ክልሎች ታጥፎ ኣንድ ክልል ከተደረጉ ጊዜ ጀምሮ የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄን ያለማቋረጥ ስያቀርብ ቆይቷል። በ1996 ዓም ሕዝቡ ሳርና ቅጠል ይዞ ሰላማዊ ሰልፍ በመዉጣት ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ለጠየቀዉ ጥያቄ የተሰጠዉ መልስ ሕዝቡን በወታደራዊ ኃይል መጨፍጨፍ እንደነበር የሚዘነጋ ኣይደለም።

ዛሬም የሲዳማ ሕዝብ በራሱ መልከአ-ምድር በሚመርጣቸዉ ተወካዮቹ አማካይነት ራሱን በራሱ ለማስተዳደርና በፌዴራል መንግስት ዉስጥ ተመጣጣኝና ተገቢዉን ዉክልና ለማግኘት እየጠየቄ ያለዉን ጥያቄ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፍትሃዊና ሕገ-መንግስታዊም ነዉ ብሎ ያምናል። ስለዚህ ይህንን ጉዳይ ኣስመልክቶ የሲዳማ ዞን ም/ቤትና የደቡብ ክልል ም/ቤት በሕገ-መንግስቱ መሰረት የወሰኑትን ዉሳኔ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ አካላት ሰላማዊና አግባብ ባለዉ መንገድ ተግባራዊ ከማድረግ ዉጪ ወደ ግጭት የሚያመራ እርምጃ ከመዉሰድ እንዲቆጠቡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ያሳስባል። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የሲዳማ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ሕገ-መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ የሚወስነዉን ማንኛዉንም ዉሳኔ የሚያከብር መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል።

ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር
ሓምሌ 08, 2011 ዓም