የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣመራር ኣካላትና በኣባላቱ ላይ የሚያካሄደውን ዛቻና እስራት በኣስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን!

የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣመራር ኣካላትና በኣባላቱ ላይ የሚያካሄደውን ዛቻና እስራት በኣስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን!

(የኦነግ መግለጫ ጥር 11 ቀን 2011 ..)

addaበትላንትናው ዓርብ (ጥር 10፡ 2011 ዓም) ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ ኣመራሮች መካከል ኣንዱ የሆኑት የኦነግ ስራ-ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ኣባልና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊዉ ኣቶ ጀቤሳ ገቢሳ፣ እንዲሁም ኣቶ ኣማን ፍሌ፣ ዶር. ቡሊ ኤጄታ፣ ደምቢ ተሾመ፣ ገልገሎ ዋርዮና እዶሳ ታደሰ የሚገኙበት የኦነግ ኣባላትና ደጋፊዎች በኢትዮጵያ መንግስት የደህነት ሃይሎች ተይዘው እስከ ኣሁን ድረስ በኢሕኣዴግ መንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ። ቀደም ባለው ቀንም (ጥር 09፡ 2011ዓም) ኮሎኔል ገመቹ ኣያናና ኣቶ ፈቀደ የተባሉ ጓደኛው በተመሳሳይ ሁኔታ ተይዘው እስከ ኣሁን ድረስ ኣልተለቀቁም። ከዚህም ሌላ ከመላው ኦሮሚያ ውስጥ የኦነግ ኣባላትና ደጋፊዎች በመሆን የተጠረጠሩ ግለሰቦች በመቶዎች ተይዘው ወደ ወህኒ እየተጋዙ ናቸው።

በዛቻና እስራት ኣስፈራርተው ሃገሪቷን እያስተዳደረ ካለው ፓርቲ የተለየ ኣመለካከት ያላቸውን ሰዎች ኣፍኖ ለመግዛት ላለፉት 27 ዓመታት ኢሕኣዴግ ያደረገው ጥረት በሺዎች የሚቆጠር የሃገር ልጆች ህይወት መሰዋትና ለመገመት ለሚያዳግት የሃብት ውድመት ከማስከተል በስተቀር ያስገኘው ውጤት የለም። ኢህኣዴግ ዛሬም ካለፈው ስህተቱ መማር ተስኖት ለውጥ ለማስገኘት ለህዝቡ የገባውን ቃል ኣፍርሶ በዛቻ፣ በእስራትና በግድያ ከሱ የተለየን የፖለቲካ ኣመለካከት በሃይል ማፈኑን እስከቀጠለበት ድረስ የሚፈለገው ሰላምና መረጋጋት ሊገኝ ኣይችልም። በህዝቦች ልጆች ውድ የህይወት መስዋዕትነት የተገኘው ይህ የለውጥ ተስፋም እንዲህ ባለው ኣካሄድ እውን ሊሆን ኣይችልም።

ህዝባችን በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸምበትን የፖለቲካ ጭቆና፣ የኢኮኖሚ ብዝበዛና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም ለዓመታት ባካሄደው መሪር ፍልሚያ ኣሁን የሚታየውን የለውጥ ጭላንጭል እድል በልጆቹ መስዋዕትነት ኣስገኘ። ዛሬ ግን “የህግ የበላይነትን ማስከበር” በሚል ስም እየተሳደዱ፣ ዛቻ እየደረሰባቸው፣ እየታሰሩና እየተገደሉ ያሉት ትላንት የነበረውን ሁኔታ ለመለወጥ መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩ ዜጎች መሆናቸው ህዝባችንን በእጅጉ እያሳዘነና እያስከፋ ያለ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ የተጀመረውን ለውጥ ያደናቅፋል እንጂ ከስኬት ኣያደርስም። በመሆኑም የኢሕኣዴግ መንግስት(የዶር. ኣብይ ኣስተዳደር) ለህዝቡ የገባውን ቃል ኣክብሮ ከተያያዘው ከዚህ የኋሊት ጉዞ እንቅስቃሴ ተገትቶ፥ እየተጣሰ ያለውን ፍትህ በማስከበር በሃገሪቷ ህዝቦች ክቡር መስዋዕትነት የተከፈተውን ይህን የለውጥ ምዕራፍ በማሳካት ከፍጻሜ ለማድረስ ወደፊት በመራመድ ድርሻውን እንዲወጣ እንጠይቃለን።

በመጨረሻም በኦነግ ኣመራርና ኣባላት እንዲሁም በደጋፊዎቻችን ላይ በኢትዮጵያ መንግስት በስፋት እየተፈጸመ ያለውን እስራትና ማስፈራሪያ ኣጥብቀን እያወገዝን፥ ይህ ድርጊት ቆሞ (ኣቶ ጀቤሳ ገቢሳና ጓደኞቹን ጨምሮ) በመላው ኦሮሚያ ውስጥ የታሰሩትም ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በኣስቸኳይ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን። ህዝባችንም (በተለይም ቄሮ) ኣይናችን እያየ በከፈልነው መስዋዕትነት የለኮስነው የለውጥ ችቦ መልሶ እንዳይጠፋና ትግላችን ወደኋላ እንዳይመለስ እንደትላንቱ ሁሉ ከያለንበት ሁሉ በኣንድነት ተነስተን ይህንን የጀመርነውን የሰላማዊ ትግል ምዕራፍ ከግቡ በማድረስ እንድንቋጨው ኦነግ ጥሪውን ያድሳል።

ድል ለኦሮሞ ህዝብ!

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር

ጥር 112011..