“ግመል ሰርቆ ኣጎምብሶ”

ABO Oromoo Gadaa“ግመል ሰርቆ ኣጎምብሶ”
ኣይደበቅ ነገር
(የኦነግ መግለጫ – ጥር 09 2011)

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት በትናንትናው ዕለት (ጥር 09 2011) በቃል-ኣቀባዩ ወይዘሪት ብልለኔ ስዩም በኩል በምዕራብ ኦሮሚያ ጦሩ ያካሄደዉን የአየር ድብደባ ለማስተባበል በማሰብ ለተለያዩ የዜና አዉታሮች የሰጠዉ መግለጫ እጅጉን ከእዉነት የራቀ ነዉ። ይህ የአየር ድብደባ ለሁለት ተከታታይ ቀናት (ጥር 4 እና 5 2011) በቄሌም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ በቄሌም ከተማና አካባቢዋ በሶስት የተላያዩ ቦታዎች ለይ ነዉ የተካሄደዉ። በዚህ ደረጃ የተካሄደዉን የአየር ድብደባ ለመካድ መሞከር ማለት “ግመል ሰርቆ ኣጎምብሶ” እንደሚባለዉ ኣይነት ልደበቅ የማይቻለዉን እዉነታ ለመደበቅ የሚደረግ ከንቱ ልፋት ነው።

ከዚሁ የአየር ድብደባ በተጨማሪም የኢሕአዴግ እግረኛ ጦር ሠራዊት በዚሁ ኣካባቢ ሰላማዊዉን ሕዝብ በመግደል፣ መኖሪያ ቤቶቹን በማቃጠል፣ ንግድ ቤቶቹን በማፈራረስና ንብረት በመዝረፍ እንድሁም ሰዎችን በጅምላ በማሰርና በማሰቃየት እኩይ ድርጊቶች ላይ ተጠምደዋል። በጊዳሚ ወረዳ ዉስጥ በአየር ሓይልና በእግረኛ ጦር በተካሄደዉ በዚህ ጥቃት እስካሁን የተረጋገጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሰባት (7) ሰላማዊ (ትጥቅ-ኣልባ) ዜጎች ሕይወት ማለፉ ታዉቋል።

ከሞቱት መካከል ኣንዷ ከአየር ወደ መሬት በሚወረወሩ ቦምቦች የፍንዳታ ድምጽ ልቧ ቆሞ የሞተች የሁለት ወር ሕጻን እንደሆነችም ታዉቋል። 8 የሕዝቡ መኖሪያ ቤቶች በእሳት ጋይቷል። 20 ንግድ ቤቶችም በኢሕአዴግ ወታደሮች ተዘርፎ ተፈራርሷል። እነዚህ በጊዳሚ ወረዳ ዉስጥ የአየር ጥቃቱ በተካሄደበት ኣካባቢ ብቻ የተፈጸሙ ናቸዉ። ግድያና ጦርነት እየተካሄደባቸዉ ባሉት በኣራቱ የወለጋ ዞኖችም በነዚሁ የኢሕአዴግ ወታደሮች የተገደሉት ሰላማዊ (ትጥቅ-ኣልባ) ሰዎች የተቃጠሉ ቤቶች፣ የተዘረፉና የወደሙ ንብረቶች ዝርዝራቻዉ በርካታ ስሆን ለወደፊቱ ተጣርቶ እንደሚዘገቡ እናሳዉቃለን።

ይህ የጠቅላይ ሚንስቴሩ ጽ/ቤት መግለጫ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) መንገድ መዝጋቱን፣ ባንኮችን መዝረፉን፣ ሕዝብን ማሰቃየቱን፣ እና ሌሎችም ፀረ-ሰላም ድርጊቶችን መፈጸሙን በማተት ለዚህ ጥቃት እንደምክንያት ያቀርባል። ይህ የመንግስት ክስ ፍጹም ከእዉነት የራቀ ነዉ። ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የተጀመረዉን የለዉጥ ሂደት ለማሳካት በሙሉ ልቡ እየሰራ ባለበት ሁኔታ የተላያዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር የስምምነታችን መንፈስ እንድደፈርስና ስምምነቱን ተግባራዊ የማድረጉ ሂደት እንድጓተት እያደረገ ያለዉ ኦነግ ሳይሆን እራሱ ኢሕአዴግ ነው። ይህ ጦርነት ኢሕአዴግ በስመ ሃገር መከላከያ ሠራዊት ለራሱ ጥቅም ያደራጀዉና እስከዛሬም ሕዝባዊ ኣለኝታነትን ያልተላበሰዉን ጦሩን ተጠቅሞ ኦነግንና የግንባሩን የፖለቲካ አመለካከት ያላቸዉን ወገኖች ለማዳከም የሚያካሄድ ጦርነት መሆኑ ለማንም ግልጽ መሆን ኣለበት።
ኦነግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተደረሰበት ስምምነት በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ሆኖ ሃገርና ሕዝቦችም ሰላም ያግኙ ዘንድ ይህ ጦርነት በኣፋጣኝ መቆም ኣለበት ብሎ ያምናል። ከዚያም በመቀጠል በመንግስት በኩል እየቀረቡብን ያሉና እኛም በበኩላችን በእኛና በሕዝባችን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ግፎች ናቸዉ የሚንላቸዉ (የሁለቱም ወገን) ስሞታና ቅሬታዎች በገለልተኛ ወገን ተመርምሮና ተጣርቶ ሓቁ እንድወጣ/እንድታይ ኦነግ ኣጥብቆ ይጠይቃል።

ድል ለኦሮሞ ሕዝብ !
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
ጥር 09, 2011